በጃል ሞሳ መሪነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሃይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ገቡ

You are currently viewing በጃል ሞሳ መሪነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሃይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ገቡ

AMN – ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም

በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ አካባቢ ታጥቀው በጃል ሞሳ መሪነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሃይሎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ገቡ።

ለበርካታ አመታት ነፍጥ አንግበው በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የህዝብን ሰላምና ደህንነት ሲያውኩ የነበሩ ከ200 በላይ የሚሆኑ የታጠቁ ሃይሎች ጋር በተደረገ ጠንካራ የመረጃ ክትትልና ውይይት ከነ ሙሉ ትጥቃቸው ወደ ሠላም እንዲመጡ መደረጉን የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዋቅጋሪ ነገራ ገልፀዋል።

ምዕራብ ዕዝ እያከናወነ በሚገኘው የግዳጅ አፈፃፀም በዞኑ በርካታ ውጤቶች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ያወሱት አቶ ዋቅጋሪ ፤ አሁን እየተመዘገቡ የሚገኙ ወታደራዊ ድሎች ለህዝባችን ከፍተኛ እፎይታን የሚያጎናፅፉ ናቸው ብለዋል።

በእሳት ተፈትኖ ክንዱ የማይዝለው ሠራዊታችን ሁሌም በድል ይደምቃል ያሉት የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለውጊያ አገልግሎት ድጋፍ ብርጋዲየር ጄኔራል ወርቅነህ ጉደታ ፤ የዋልታ ኮር ክፍለ-ጦሮች በየጊዜው የሚያስመዘግቡት አንፀባራቂ ውጤትም የዚሁ እውነታ አንዱ ማሳያ ሥለመሆኑም ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ፍላጎታቸውን በሃይል ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች የህዝብን ሰላም ለማሳጣትና የሃገራችንን ልማት ለማደናቀፍ ቢፍጨረጨሩም አይሳካላቸውም ያሉት ብርጋዲየር ጄኔራል ወርቅነህ ጉደታ፤ የሌሎች ሃገራትን አጀንዳ ይዘን ከመጋጨት መውጣት የሰላም አምባሳደር መሆን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል። ሃገር የምትፀናውና የምትበለፅገው በአንድነትና በጋራ ስንቆም መሆኑን በመጠቆም።

ምዕራብ ዕዝ በማይነጥፍ የጀግንነት ጉዞው የሃገራችንን ሰላምና የህዝባችንን ደህንነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ የጠቆሙት የዋልታ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል አዘነ ሽመልስ ፤ ሌሎች ተመሳሳይ ሃይሎችም በዚሁ መንገድ ቢመጡ በሠላም ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዕለቱ የዕዝ፣ የኮር፣ የምስራቅ ወለጋ ዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች መገኘታቸውን የመከላከያ ሰራዊት ለኤ ኤም ኤን የላከው መረጃ ይጠቁማል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review