የዓድዋ ድል መታሰቢያ የታሪክ እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየትና የወል ትርክትን በምርምር ለመገንባት የሚያስችለውን የጋራ ስምምነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር ተፈራረመ።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የዓድዋ ድል የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራትና የፓን አፍሪካኒዝም ምልክት ነው። ይህንን ታላቅ ታሪክ ለማስቀጠልና የወል ትርክትን ለመገንባት በጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቱ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) መታሰቢያው ከአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለመሥራት መወሰኑ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን አንስተው፤ ታሪክን በሚገባው ቦታ ለማቆየትና ለትውልድ ለማሻገር ተቋማቸው በትምህርትና በቴክኖሎጂ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መታሰቢያው ኢትዮጵያን ለዓለም የምናስተዋውቅበት ታሪክ ነጋሪ ተቋም መሆኑን ገልጸው፣ በቴክኖሎጂና በፈጠራ የበለጸጉ ተማሪዎችን በማሳተፍ ሀገራዊ ገጽታን የመገንባት ሥራ በጋራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ሙሉጌታ( ዶ/ር) የተዛቡ የታሪክ ንግግሮችን ማስተካከል የሚቻለው በትምህርት ተቋማት መሆኑን ተናግረው፣ ዩኒቨርሲቲው ይህንን የታሪክ ማስተካከያ ዕድል በማግኘቱ ያለውን ደስታ ገልጸዋል።
ይህ ስምምነት መታሰቢያውና ዩኒቨርሲቲዎቹ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ በመሥራት የዓድዋን ታሪክ በሳይንሳዊ መንገድ ለዓለም ለማስተዋወቅና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።
በፀጋ ታደለ