የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ተወያየ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ተወያየ
  • Post category:ፖለቲካ

AMN ታኅሣሥ 13/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሠሌዳን ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ባስተዋወቀበት ወቅት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ከተነሡት ጥያቄዎች ውስጥ “የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ ይቅር/ይታገድ” የሚለውና “ከገዢው ፓርቲ ጋር መወያየት እንፈልጋለን” የሚሉት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።

ቦርዱ ከፓርቲዎች የተነሡት ጥያቄዎች መልስ ሊያገኙ በሚችሉበት አግባብ ሲሠራ የቆየ ሲሆን፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባው “የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ” ሊታገድ ችሏል። ቦርዱ በዛሬው ዕለት ታኅሣሥ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. 7ኛው ጠቅላላ ምርጫን አስመልክቶ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በውይይቱ መክፈቻ ንግግራቸውም መድረኩ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ እንዲሆን ከማን ምን ይጠበቃል፣ አስቻይ የፖለቲካ ምኅዳር መፍጠርን፣ እንዲሁም የውይይቱ ቀጣይነት በምን መልኩ መሆን አለበት የሚለውን የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ባሉበት መወያየት አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ አብራርተው፤ በቦርዱ እስካሁን የተሠሩ ሥራዎችን እንዲሁም በመሠራት ላይ ያሉት ላይ ማብራሪያ ሰጥተው ተሣታፊዎቹ ምርጫውን አስመልክቶ ያሏቸውን ማንኛውም ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ መድረኩን ለተሣታፊዎች ክፍት አድርገዋል።

የመክፈቻ ንግግሩን ተከትሎ ተሣታፊ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ የዕጩ ድጋፍ ፊርማ ማቅረብ መታገድን እና የመድረኩ መዘጋጀትን አስመልክቶ ለቦርዱ ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፤ ምርጫውን አስመልክቶ መሟላት አሉባቸው ያሏቸውን ሁነቶች፣ አስቻይ ሁኔታና የውይይቱ ቀጣይነትን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች ላይ ተሣታፊ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያሏቸውን አስተያየቶችና ጥያቄዎች አጋርተዋል።

ሜላትወርቅ በውይይቱ ማጠቃለያ ንግግራቸው ፓርቲዎቹ ለሰጡት አስተያየትና ላቀረቡት ጥያቄዎች አመስግነው፤ የፀጥታ አስቻይ ሁኔታን በተመለከተና ሌሎች ምርጫውን የተመለከቱ ጉዳዮችን አስመልክቶ የሚኖሩ የምክክርና የውይይት መድረኮች ቀጣይነት ያላቸው እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

የአስፈጻሚዎችን ገለልተኝነት አስመልክቶ ለተነሣው ጥያቄ ቦርዱ ዝርዝራቸውን ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ መላኩን አስታውሰው በገለልተኝነቱ/ቷ ላይ ጥያቄ ያላቸው አስፈጻሚ ካገኙ ዝርዝሩን እንዲልኩ ቦርዱ በመጠበቅ ላይ መሆኑን፤ በተመሳሳይ መልኩ ለፓርቲዎች በጀት ለማከፋፈልም ፓርቲዎቹ ሠነድ እንዲያቀርቡለት በመጠበቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ተሣታፊዎቹ ያነሡት ሌላኛው ጥያቄ “በትግራይ ምርጫ ይካሄዳል ወይ” የሚለው ሲሆን፤ ሜላትወርቅ በምላሹ ቦርዱ በሌሎች ክልሎች አንደሚያደርገው በትግራይ ክልልም ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን፤ ባሳለፍነው ሣምንትም ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በትግራይ ክልል ምርጫ ስለሚካሄድበት ሁኔታ እንደተወያዩና ቦርዱም ውይይቱን ተከትሎ ጥሩ ውጤት እንደሚጠብቅ መናገራቸዉን ከቦርዱ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review