ተቋማት ሰላምን የዕቅዳቸው አካል በማድረግ ለሰላም ግንባታ አሻራቸውን ማስቀመጥ እንደሚገባቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሰላም ሚኒስቴር ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በመተባበር የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች የህግ ማውጣት፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች ሲያከናውኑ የሰላም አካቶ ትግበራን እውን ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ እና ሌሎችም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና እንግዶች ተገኝተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፤ ሰላም የሁሉም ዋነኛ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የሰላም ግንባታ ጉዳይ በሁሉም ዕቅዶች፣ በፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መካተት ይኖርበታል ብለዋል።
ተቋማትም የሰላም ግንባታን የዕቅዳቸው አካል በማድረግ ለአዎንታዊ ሰላም (Positive peace) ግንባታ አሻራቸውን አስቀምጠው መሄድ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ተቋማት የግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን መከላከልና ማስቀረት በሚያስችል መንገድ መሥራት አለባቸው ብለዋል።
እንዲሁም ህግና ስርዓትን ያልተከተሉ አካሄዶችን በማስተካከል፣ የፕሮጀክቶች አፈፃፀምን በማላቅ፣ አሳታፊነትን በማጎልበት ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን ማፅናት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የግጭት ጥንስሶችን ከስር መሰረታቸው ለማጥፋት ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ስራዎችን በጊዜና በጥራት ማጠናቀቅ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
የተቋማት ስራዎች የግጭት መንስኤዎች መሆን የለባቸውም ያሉት ዶክተር ቢቂላ፤ ግጭትን መከላከልና ሰላም ግንባታ ላይ መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የሰላም ግንባታ በግብርና በጤና እና በሌሎችም ተቋማት እንዴት ይካተት ለሚለው ራሱን የቻለ ሰነድ ሊዘጋጅለት ይገባል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡