የሥነ-ምግባር ጉድለቶች በታየባቸው 179 አመራርና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መዉሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ

You are currently viewing የሥነ-ምግባር ጉድለቶች በታየባቸው 179 አመራርና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መዉሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ

‎AMN – ታኅሣሥ 13/2018 ዓ.ም

‎የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ባለፉት አምስት ወራት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ባከናወናቸው የሪፎርም ስራዎች፣ የስነ-ምግባር ጉድለት ባለባቸው 179 አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

‎የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለጹት፣ ቢሮው የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት ባለፉት አምስት ወራት ሰፋፊ የአደረጃጀት፣ የቴክኖሎጂ እና የሰው ሀብት ልማት ስራዎች አከናውኗል ።

‎ቢሮው በዘረጋው የአሰራር ማሻሻያ ለብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱና ለውሳኔ አሻሚ የሆኑ አሰራሮችን ለማስቀረት 24 አዳዲስ አሰራሮች ተዘርግተው ወደ ተግባር ገብተዋል ብለዋል ።

‎የዲጂታል ኢኮኖሚውን ውጥንን ለማሳካትና የግብር አሰባሰቡን ለማዘመን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በውስጥና በውጭ አቅም እንዲለሙ መደረጋቸውንም አስረድተዋል።

‎በተለይም የቁጥጥር ስራውን በካሜራ ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ግልጽነትን ለመፍጠር ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

‎ሰራተኛው የአገልጋይነት ስብዕና እንዲላበስና ለግብር ከፋዮች ተገቢውን ክብር እንዲሰጥ የአመለካከትና የክህሎት ስልጠናዎች መሰጠታቸውን ገልጸዋል።

‎ዳይሬክተሩ አጽንኦት ሰጥተው እንደገለጹት፣ ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠትና ተገልጋይን ማመናጨቅ የስነ-ምግባር ችግር በመሆኑ ይህንንም ለማረም የተጠያቂነት ስርዓት ተዘርግቷል ብለዋል።

‎በዚህ መሰረት ባለፉት አምስት ወራት ተገቢውን አገልግሎት ባለመስጠትና በተለያዩ የሥነ-ምግባር ግድፈቶች ውስጥ የተገኙ 179 አመራሮችና ባለሙያዎች ተጠያቂ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

‎ተጠያቂ ከተደረጉት መካከል 20 የሚሆኑት በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አመራሮች መሆናቸውን አስረድተዋል።

‎እነዚህ እርምጃዎች በዋነኝነት በፍትሐዊነት ገቢን ለመሰብሰብና ቢሮው ከብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ ለማደራጀት የሚረዱ መሆናቸውን አቶ ሰውነት አየለ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ገልፀዋል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review