የፕላስቲክ ከረጢቶችን በሚያመርቱ እና በሚጠቀሙ አካላት ላይ የህግ ተጠያቂነት ድንጋነጌዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ

You are currently viewing የፕላስቲክ ከረጢቶችን በሚያመርቱ እና በሚጠቀሙ አካላት ላይ የህግ ተጠያቂነት ድንጋነጌዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ
Plastic bag

AMN – ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም

ከጥር 23 ጀምሮ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን በሚያመርቱ እና በሚጠቀሙ አካላት ላይ የህግ ተጠያቂነት ድንጋነጌዎች ተፈፃሚ እንደሚሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የፕላስቲክ ክልከላን የሚደነግገው አዋጅ ለአምራቾች ከተሰጠው የ6 ወራት የሽግግር ጊዜ በኋላ ከጥር 23 ቀን 2018 ጀምሮ አዋጁ ተግባራዊ እንደሚደረግም ባለስልጣኑ ገልጿል። በደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ አተገባበር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ ፣ ባለስልጣኑ በአካባቢ ጥበቃ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ መንግስት የከተሞችን ደረጃ ለማሳደግ እየሰራ ያለውን የልማት ስራ ሁሉም ሊደግፍ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ የወንዝ ዳርቻ እና ሌሎችንም የልማት ስራዎች ለመደገፍ አንድ ጊዜ ተጠቅመን የምንጥላቸው የፕላስቲክ ምርቶች እንቅፋት ስለሚሆኑ አዋጁን መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።

ቀደም ሲል በዚሁ የፕላስቲክ ምርቶች ማምረት ላይ ተሰማርተው የቆዩ አምራቾችም ወደ ሌላ ዘርፍ መሰማራት እንዲችሉ በጋራ ሲሰራ መቆየቱንም ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።

የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ማምረት፣ ወደ ሀገር ማስገባት እና መሸጥን በህግ እንደሚከለክል ተገልጿል፡፡

የወጣውን አዋጅ ለማስተግበር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ በመድረኩ ላይ ጥሪ ቀርቧል።

በመሀመድኑር ዓሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review