ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ፈጠራን መሰረተ ልማት ያደረገ እና በሁሉም መስክ ሉዓላዊ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተነደፈ ሀገራዊ ትልምና ራዕይ ነው

You are currently viewing ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ፈጠራን መሰረተ ልማት ያደረገ እና በሁሉም መስክ ሉዓላዊ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተነደፈ ሀገራዊ ትልምና ራዕይ ነው

AMN – ታኅሳስ 14/2018 ዓ.ም

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የሀገሪቱን የዲጂታል ሽግግርን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በመንግሥት አሥተዳደር ማዕቀፍ ዉስጥ ለማካተትና በእስካሁኑ የተመዘገቡ የኢኮኖሚ ስኬቶችን ይበልጥ ለማጠናከር የተነደፈ ሀገራዊ ራዕይ ነዉ፡፡ ይህም ሁሉን አቀፍ እድገት እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ታሳቢ አድርጓል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው ይህ የትግበራ ስትራቴጂ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 መሠረት ላይ የተገነባ፣ ከአስር ዓመት የልማት ዕቅድ እና ከሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ጋር የተጣጠመ ነው፡፡

በስትራቴጂው ቴክኖሎጂ እንደ አካታች እድገት እና ተወዳዳሪነት እንደ አንቀሳቃሽ ሞተር ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የልማት ስትራቴጂ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ማሸጋገር ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን፣ በተለይም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዋና ዋና ጉዳዮች የዲጂታል ስራ ፈጣሪነትን ማሳደግ፣ የኢኮኖሚ አካታችነትን ማረጋገጥ እና በሁሉም ዘርፎች ሉዓላዊነት የተጠበቀበት ዲጂታል ኢትዮጵያን እዉን ማድረግ ነዉ፡፡

ይህ ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎችን የያዘ ሲሆን፣ ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል እድሎችን መፍጠር እና በተቋማት እና በዜጎች መካከል መተማመንን መገንባት ነዉ፡፡ የዲጂታል ተደራሽነትን በተለይም በከተማ እና በገጠር ማህበረሰቦች መካከል ያለዉን ልዩነት ለማጥበብና አንድ የማድረግ፣ እንዲሁም ወደፊት የዲጂታል ፈጠራ አሳቢ ትዉልድን ለማፍራት ፈጠራን መሰረተ ልማት ያደረገ ትልም ነው ፡፡

ስትራቴጂው የሳይበር ደህንነት፣ የውሂብ (ዳታ) ጥበቃ እና የመንግሥት ተቋማት የመቋቋም አቅምን ከፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ዘለቄታ ያለዉ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግርን እዉን ለማድረግ የታለመ መሆኑ ነዉ፡፡

በተጨማሪም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቶች በቴክኖሎጂ እንዲሻሻሉ፣ የኢኮኖሚ ልዩነቶችን ማጥበብ እና ማኅበራዊ አካታችነትን ለማረጋገጥም አይተኬ ሚና አለዉ፡፡

በተለይም ዲጂታል መሳሪያዎችን በግብርና፣ በፋይናንስ፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች ዘርፎች ውስጥ በማካተት፣ የሀገሪቱን ምርታማነትን ለመጨመር እና ፍትሃዊ ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ ያለዉ መሆኑ ታምኖበታል፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዕቅድ የቴክኖሎጂ ስታራቴጅክ ዕቅድ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ሕይወት በተጨባጭ የሚቀይር እና የመንግሥት ጽኑ የብልጽግና መሻት የሚያረጋግጥ ተግባራዊ መግለጫ ተደርጎ የሚታይ ነው፡፡

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ውጥን የኢትዮጵያን እሴትንና ማንነትን በመጠበቅ የሀገር በቀል ዲጂታል ፈጠራ ሥራዎችን ለኢኮኖሚ እድገት ማዋል የሁሉንም ርብርብና ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡

በአጠቃላይ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትልም መሳካት ውስጣዊ ጥንካሬን ማጎለበት፣ከአለም ጋር በኢኮኖሚ መተሳሰር፣ በሁሉም ዘርፎች ትብብርን ማሳደግ ፣ ፈጣን ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ለውጥን የመላመድ አቀምና ችሎታን ማላቅን ጨምሮ መፍጠርና መፍጠን እንደሚጠበቅ የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለኤ ኤም ኤን በላከው መግለጫ ግልጿል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review