በ90 ቀናት ውስጥ ለ115 ሺህ ስራ ፈላጊ ወጣቶች እና ሴቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሠራ የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ ።
የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ የ2018 በጀት አመት እስከ የካቲት 30/2018 ዓ.ም የሚከናወን የስራ ዕድል ፈጠራ የ90 ቀናት የንቅናቄ ዕቅድ መወያያ መድረክ አካሂዷል ።
በዕቅድ ወይይቱ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ እና በብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት ም/ሀላፊ እና የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ ወ/ሮ አለምፀሀይ ሽፈራው ጨምሮ የክፍለ ከተማ ስራና ክህሎት ፅ/ቤት ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

በመድረኩ በስራ እድል ፈጠራ 115 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እና በከተማ ግብርናና በሌማት ቱሩፋት 1.1 ሚሊየን ተጠቃሚዎችን የማስቀጠል እና አዳዲስ 122 ሺህ ተጠቃሚዎችን ወደ ስራ የማስገባት መታቀዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ ገልጸዋል፡፡
”በከተማዋ ያሉ የስራ ዕድሎችን በእጥፍ በማሳደግ ስራ ፈላጊ ወጣቶች እና ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፖርቲ ቅ/ጽ/ቤት ም/ሀላፊ እና የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ ወ/ሮ አለምፀሀይ ሽፈራዉ ተናግረዋል ።
የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የመልካም አስተዳድር ስራዎችን እንዲሁም ያልተጠናቀቁ ስራዎችን በጊዜ መጨረስ ይገባል ሲሉም አክለዋል ።
በወንድምአገኝ አበበ