የመደመር መጽሐፍት ሞባይል መተግበሪያ ምን አካቷል?

You are currently viewing የመደመር መጽሐፍት ሞባይል መተግበሪያ ምን አካቷል?

AMN- ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም

የመደመር መጽሐፍት ሞባይል መተግበሪያ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ቋሚ ዘጋቢዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም መጽሃፉን አስመልክቶ በሰጡት ገለጻ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተጽፈዉ ለንባብ ከበቁ መደመር፣ የመደመር መንገድ፣ የመደመር ትውልድና የመደመር መንግሥት መጽሃፍት መካከል ሶስቱ መጽሃፍት ከሕትመት ባሻገር በመደመር መተግበሪያ አማካኝነት በድምጽ ተተርከው መቅረባቸዉን ገልጸዋል፡፡

አራቱ መጽሐፍት በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ እንዲሁም ‘መደመር’ እና ‘የመደመር ትውልድ’ ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መዘጋጀታቸዉን የተናገሩት ኃላፊዋ ከነዚህ መካከል ሶስቱ መጽሐፍት በተለይ አይነ ስውራን ማዕከል አድርገዉ በድምጽ ተተርከዉ መቅረባቸዉን ገልጸዋል፡፡

መጽሐፍቱ በሞባይል መተግበሪያ ተዘጋጅተዉ መቅረባቸዉ የመደመር ሃሳቦች ድንበር ተሻግረዉ የሁሉም እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፡፡

በዉጭ ሃገራት የሚኖሩና መጽሐፉን አግኝተዉ የማንበብ እድል ያገኙ ሰዎች ቢኖሩም አሁን ላይ መጽሀፉ በድምጽ ፎርማት መቅረቡ የመደመር እሳቤዎችን ብቻ ሳይሆን የተሰሩት ስራዎችን በምን መርህ እንደተከናወኑ ለመረዳት ያስችላሉ ብለዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም የሞባይል መተግበሪዉ በሁለት ፎርማት ወይም አማራጮች መቅረባቸዉንም አብራርተዋል፡፡

አንደኛው የአይፎን (iPhone) ተጠቃሚዎች በ iOS ላይ በመግባት ‘መደመር’ የሚለውን መተግበሪያ ዳውንሎድ በማድረግ እንዲሁም አንድሮይድ (Android) ስልክ ያላቸው ደግሞ ፕሌይ ስቶር (Play Store) ላይ ገብተው ዳውንሎድ ማድረግ ይችላሉ፡፡

የስማርት ፎን (Smart phone) ተደራሽ ያልሆነባቸዉ አካባቢዎች ካሉ በዴስክቶፕ፣ በኮምፒውተር ወይም በላፕቶፕ በ’መደመር’ ድረ-ገጽ (Website) ላይ መጽሐፉን ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

በድምጽ ተተርከዉ ከቀረቡ ሶስቱ የመደመር መጽሐፍት በተጨማሪ ከመጽሐፍቱ የተመረጡ አጫጭር የፎቶ ጥቅሶች (Photo quotes) እና ቪዲዮዎች መካከተታቸዉን አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ጊዜያት የመደመር መጽሐፍትን አስመልክቶ የተናገሯቸዉ ንግግሮች በአጫጭር ቪዲዮች ጭምር በመደመር መጽሐፍት ሞባይል መተግበሪያ ተካተዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review