በየመንገድ ዳር የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች እና የመሥሪያ ቤት መግቢያ አጥሮች ላይ ይለጠፉ የነበሩ ማስታወቂያዎችን ያስቀረው አሰራር

You are currently viewing በየመንገድ ዳር የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች እና የመሥሪያ ቤት መግቢያ አጥሮች ላይ ይለጠፉ የነበሩ ማስታወቂያዎችን ያስቀረው አሰራር

AMN- ታኅሣሥ 15/2018

በአዲስ አበባ ከተማ ከጥቂት ዓመታት በፊት በየአጥሮቹ፣ በየኤሌክትሪክ ምሰሶዎቹ እና በየመሥሪያ ቤት መግቢያዎች ላይ የአካባቢን ገጽታ የሚያጎድፉ የተዘበራረቁ ማስታወቂያዎችን መመልከት የተለመደ ነበር።

ከተማዋ በተለይም በኮሪደር ልማቱ የተላበሰችውን አዲስ ገጽታ እና የ(ስማርት ሲቲ) ጉዞዋን ተንተርሶ ብቅ ያለው የዲጂታል ማስታወቂያ ሥርዓት አዲስ መልክ ሆኗታል። ዲጂታል ማስታወቂያ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚፈጸም ፈጣንና ውጤታማ የማስታወቂያ መንገድ ነው።

የንግድ እንቅስቃሴዎች፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች ምርታቸውን፣ አገልግሎታቸውን ወይም መልእክታቸውን ለሰዎች ለማሳወቅ ይጠቀሙበታል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለሥልጣን የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ አሰጣጥ አንዱ ኃላፊነቱ መሆኑን ተከትሎ፣ በከተማዋ ከዚህ ቀደም ለእይታ ሳቢነት የሌላቸውንና አካባቢን የሚበክሉ የማስታወቂያ መንገዶችን ከመቆጣጠር አንጻር ስራዎችን በስፋት መስራቱን ይገልጻል።

ይህ የዲጂታል ማስታወቂያ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ እና ለእንግዶቿ የሚመጥን ገጽታን ከማላበስ ባለፈ፣ ነዋሪዎች በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ዓበይት ሁነቶች ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንዲሁም እንግዶች የቱሪዝም መዳረሻ እና መስህብ ስፍራዎችን እንዲያውቁ የራሱን ሚና እያበረከተ መሆኑን የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አበበ እሸቱ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የማኅበረሰቡን እሴት ባልጠበቀ መልኩ ሲለጠፉ የነበሩ ማስታወቂያዎችን ለመቀየር፣ ዲጂታል ማስታወቂያዎች የኮሪደሩ አካል ተደርገው እየተሰሩ የሚገኙ መሆኑን በማመላከት፣ የዲጂታል ስክሪኖቹ ለከተማዋ አዲስ ገጽታ ፈጥረዋል ብለዋል።

ከውጭ ለሚመጡ መሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክቶችን በማስተላለፍና የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

ዲጂታል ማስታወቂያ ከውበት በተጨማሪ በርካታ መልእክቶችን በአጭር ጊዜ ተደራሽ ከማድረግና ድግግሞሽን ከመቀነስ አንፃር ተመራጭ እንደሆነም አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ቢኒያም ታዬ በበኩላቸው፣ የዲጂታል ማስታወቂያ ስክሪኖች የከተማዋን ገጽታ መቀየራቸውን ጠቅሰዋል።

ይህ ወጥነት ያለው መደበኛ አሰራር እንዲኖረው እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ መለያ እና መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑንና የሚለቀቁ ማስታወቂያዎችም ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review