ከህብረተሰቡ ባህል፣ ሞራልና እሴት ተቃራኒ የሆኑ መልዕክቶችን በማህበራዊ ሚዲያ ሲያሰራጭ የነበረን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ፡፡
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ተማ ወረዳ 6 ነዋሪ የሆነዉ ናትናኤል ባደግ ገብሬ የተባለዉ ተጠርጣሪ ማህበራዊ ሚዲያዎችን (YouTube እና tiktok platform) ን በመጠቀም ጾታን መሠረት ያደረጉ አፀያፊ መልዕክቶችን ሲያሰራጭ መቆየቱን ፖሊስ አስተዉቋል።
ተጠርጣሪው በተለምዶአዊው ንግግር ሊገለፁ የማይችሉ አስፀያፊ ቃላትን በመጠቀም በትውልዱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ እና መሰል ይዘቶችን በተደጋጋሚ ጊዜ በመስራት በማህበራዊ ሚዲያ (YouTube እና tiktok platform) በመጠቀም ሲያሰራጭ እንደነበር ፖሊስ አብራርቷል፡፡
ፖሊስ በቁጥጥር ስር በዋለው ናትናኤል ባደግ ወይም “የማህበራዊ ሚዲያ አንቂ ወይም ይዘት ፈጣሪ ነኝ” በሚለው ግለሰብ ላይ ምርመራ ጀምሯል።
አንዳንድ ኃላፊነት በማይሰማቸው ግለሰቦች በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከህብረተሰቡ ሞራል ባህልና እሴት ባፈነገጠ ሁኔታ አሉታዊ መረጃዎች እየተሰራጩ መሆኑን ፖሊስ አስታዉቋል።
በቀጣይም በማህበረሰቡ በተለይም ታዳጊ በሆኑ ህፃናት ሥነ-ልቦናና ሞራል ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሱና ተመሳሳይ ድርጊት ውስጥ በሚገቡ ግለሰቦች ላይ ተገቢውን ህጋዊ ርምጃ እንደሚወስድም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አሳስቧል።