የአዲስ አበባ ከተማ ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን በመዲናዋ የሚከናወኑ ሰው ተኮር ስራዎችንና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የሁሉንም ነዋሪ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችለውን ደንብ 161/2016ን ይፋ አድርጓል።
ኮሚሽን ባዘጋጀው የበጎ ፍቃድ አገልግሎትና የማህበራዊ ኃላፊነት ደንብ ዙሪያ ከአዲስ አበባ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ለሐይማኖት አባቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሒዷል።
በአዲስ አበባ በህዝብና በመንግስት ተሳትፎ በተሰሩ ሰው ተኮር ስራዎች የበርካታ ዜጎችን ችግር መቅረፍ መቻሉን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ይመር ከበደ ገልጸዋል።
በጎ ፈቃድን ባህል ለማድረግና የዜጎችን ችግር ለማቃለል የህብረተሰቡን በጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳትፎን ማሳደግና በህግ መምራት በማስፈለጉ ደንቡ መውጣቱን ተናግረዋል።
በደንቡ ዙሪያ የኃይማኖት አባቶች ግንዛቤን በመያዝ የየእምነቱ ተከታዮች ከዚህ ቀደም የሚያደርጉትን የተቸገሩ ወገኖችን በድንበር፣ በሐይማኖትና በብሔር ሳይገደቡ የሚያደርጉትን የበጎነት ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ እንዲያስተምሩም ጠይቀዋል።

መንግስትና የሐይማኖት ተቋማት በማህበራዊና ሰብአዊ ስራዎች ላይ ተቀናጅተው ከሰሩ የዜጎችን ችግር ምን ያህል መቅረፍ እንደሚቻል በአዲስ አበባ የተሰሩ ሰው ተኮር ስራዎች ማሳያ ናቸው ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና-ጸሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ ናቸው።
የዜጎችን ማህበራዊ ቸግር መቅረፍ ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን የህዝብ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ያሉት መጋቢ ታምራት ለዚህም የሐይማኖት ተቋማት ማህበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣ በስነ- ምግባር የታነጸ ትውልድን በማፍራት በኩል ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

የሐይማኖት ተቋማት ለሰብአዊ ልማትና ለትውልድ ሞራል ግንባታ መሰረት ናቸው ያሉት ዋና ጸሐፊው ጉባኤው የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማትን በማስተባበር በ20 ቢሊየን ብር ወጪ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ይሰራል ብለዋል።
በአዲስ አበባ የተማሪዎች ምገባን ጨምሮን በርካቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰዉ ተኮር ስራዎች የህዝብን ችግር እየፈቱ መሆኑን በግል የሚታይ ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው ሁሉም በዚህ በተቀደሰ የበጎ ፈቃድ ተግባር እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሔናክ ዘነበ