የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በአዲሱ የመረጃ ነፃነት ረቂቅ ህግ ላይ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በቀደመው አዋጅ ላይ የነበረው ሥልጣን የተሟላ አለመሆኑ፣ የመረጃ ነፃነት አፈጻጸምን ደካማ አድርጎት መቆየቱ በጥናት በመለየት የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ማሻሻያው አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተገልጿል።
በማሻሻያው መሠረት የተካተቱ አዳዲስ ድንጋጌዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።
የምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ አባል ጋዜጠኛ መሰረት አታላይ የተሻሻለው የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጅ መረጃ ሲጠየቁ አልሰጥም የሚሉ ኃላፊዎች እንደ በፊቱ በተቋም ደረጃ ሳይሆን፣ በግለሰብ ደረጃ በሕግ ተጠያቂ እንዲደረጉ የሚያስገድድ አንቀጽ በማሻሻያ ረቂቁ ማካተቱ ለተጠያቂነት በጎ አበርክቶ ያለው መሆኑን እና ተጨማሪ አንቀጾች መካተታቸውን በበጎ አንስተዋል ።
ነገር ግን መረጃ ላለመስጠት የሚቻልባቸው ተብለው የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች መብዛታቸው ለተግባራዊነት ስጋትም እንደሚሆን ተናግረዋል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ ሊሻሻሉ ይገባል የተባሉ በርካታ ሀሳቦች በምክር ቤቱ የቀረቡ ሲሆን ጥሪ የተደረገላቸው የውይይቱ ተሳታፊዎችም በረቂቁ ላይ ውይይት እያካሄዱ ይገኛሉ።
በቤተልሔም አየነው