የህዝብ ውይይቶቹ በመንግስት እና በህዝብ መካከል ጠንካራ መግባባት የፈጠሩ ስኬታማ መድረኮች ነበሩ

You are currently viewing የህዝብ ውይይቶቹ በመንግስት እና በህዝብ መካከል ጠንካራ መግባባት የፈጠሩ ስኬታማ መድረኮች ነበሩ
  • Post category:ፖለቲካ

AMN- ታኀሣሥ 16/2018 ዓ.ም

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ሲካሄዱ የነበሩ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች በመንግስት እና በህዝብ መካከል ጠንካራ መግባባት የፈጠሩ ስኬታማ መድረኮች እንደነበሩ በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጹ፡፡

አቶ ሞገስ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፣ በውይይቱ ከህዝብ የሚነሱ የተለያዩ ጉዳዮችን በማድመጥ ለመንግስት ሥራዎች በግብዓትነት ለመጠቀም የሚያስችል ዘርፈ ብዙ ሀሳቦች የተነሱበት እና ስኬት የታየበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ ከከተማ እስከ ብሎክ ድረስ ህዝቡን በነቂስ ያሳተፈ መሆኑን የገለጹት አቶ ሞገስ፣ የመንግስት ሥራዎች ባለቤት ህዝቡ በመሆኑ የሚሰጡ አስተያየቶችን እንደ ግብዓት መጠቀምና ለህዝቡ ግልጽ መረጃ ማድረስ የመድረኩ ዋና ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በተጀመረው የሰላምና የልማት ጉዞ ላይ እንቅፋት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እኩይ ተግባርን ህዝቡ ተገንዝቦ እንዲያወግዛቸው እና ሕዝቡ በቀጥታ የመረጃ ባለቤት እንዲሆን ለማስቻል መሆኑንም አንስተዋል።

የምክክር መድረኩ “ቀደም ሲል ከነበሩት ፕሮፓጋንዳ ተኮር መድረኮች በተለየ፣ የተሰሩ ስራዎችን ለመገምገም እና የጎደሉትን ለማረም የሚያስችሉ የምክክር መድረኮች በመሆናቸው ህብረተሰቡ ከፍተኛ ፍላጎት ያሳየበት መሆኑን ኃላፊው ገልፀዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጉባ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያበሰሩት ብስራት፤ ሀገሪቱን ወደ ሌላ ምዕራፍ የሚያሸጋግር በመሆኑ ቀጣይ የቤት ሥራዎች ላይ ከህዝቡ ጋር ሰፊ ምክክር ተደርጓል።

እነኚህ ብስራቶች ምን ምን ጉዳዮችን አካተዋል፣ እንዴት ይተገበራሉ፣ ከህዝብ እና ከመንግስት ምን ይጠበቃል የሚለውን ከህዝቡ ጋር በጥልቀት ውይይት መደረጉ አቶ ሞገስ ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ በሁሉም የከተማዋ ክፍለ ከተሞች፣ ወረዳዎችና ብሎኮች በከፍተኛ አመራሮች መሪነት የተካሄደ ሲሆን፣ ህዝቡም መንግስት ለጀመራቸው ሁለንተናዊ የብልጽግና ስራዎች እውቅና የሰጠበት እንደነበር አውስተዋል።

በመጨረሻም ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻውን ለመወጣት ቃል የገባበት መድረክ መሆኑን አቶ ሞገስ ባልቻ አረጋግጠዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review