አባቴ በህግ ትምህርት ሲጠብቀኝ እኔ ደግሞ በሙዚቃ ትምህርት ውስጥ ተገኘሁ

You are currently viewing አባቴ በህግ ትምህርት ሲጠብቀኝ እኔ ደግሞ በሙዚቃ ትምህርት ውስጥ ተገኘሁ

AMN – ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም

ታዋቂው የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ እና የዜማ አቀናባሪ አርቲስት አኒስ ገቢ፣ ስለ ሙዚቃ ህይወቱ እና ከአባቱ ከአንጋፋው አርቲስት ገቢ ኤዳኦ ጋር ስላለው ግንኙነት ከኤ ኤም ኤን ፕላስ (AMN PLUS) ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል፡፡

የአርቲስት አኒስ ገቢ አባት አርቲስት ገቢ ኤዳኦ ልጃቸው በህግ ትምህርት ተመርቆ የህግ ባለሙያ እንዲሆንላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም፣ አርቲስቱ ግን በአባቱ ስራዎች በመማረክ ከልጅነቱ ጀምሮ የገባበት የሙዚቃ ፍቅር ወደ አርቱ እና ሥነ ጥበቡ ዓለም እንዲያዘነብል አድርጎታል።

አርቲስት ገቢ ኤዳኦ የመድረክ ስራ ሲኖራቸው ልጃቸውን አኒስ ገቢን ይዘውት ይሄዱ እንደነበር ገልጾ፣ ልጃቸው አኒስ ገቢም በዚሁ መንገድ በሙዚቃ ፍቅር እንደተያዘ ተናግሯል።

አርቲስት አኒስ አባቱ ሳይሰሙ ሙዚቃን በድብቅ ሲያጠና ቆይቶ፣ በመመረቂያው ቀን አባቱ ልጃቸው በሙዚቃ ጥበብ መመረቁን ሲያውቁ እጅግ መገረማቸውንና መደሰታቸውን አንስቷል።

አንጋፋው አርቲስት ገቢ ኤዳኦ ቀደም ሲል በሰጡት ሃሳብ፣ በሙዚቃው ዘርፍ በነበሩት ተግዳሮቶች ተስፋ በመቁረጥ እራሳቸውን ከሙዚቃው ዓለም አግልለው እንደነበር እና፣ “ልጄ አኒስ ደርሶልኝ እና የሙዚቃ ሙያውን በሳይንሳዊ እና በዘመናዊ መንገድ ተምሮ ወደ ሙዚቃ ሥራዬ እንድመለስ አድርጎኛል” ሲሉ ተናግረው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ላይ አባትና ልጅ የጥበብ ስራዎቻቸውን በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጿል።

አርቲስት አኒስ የሙዚቃ ትምህርትን አስፈላጊነት ሲናገር “እግራችንም ቢሆን ስለሰለጠነ ነው የሚራመደው” ሙዚቀኞችም የሙዚቃ ሙያቸውን በዘመናዊ ትምህርት መደገፍ እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡
ሙዚቃችን መድረስ ከሚጠበቅበት ደረጃ ላይ አልደረሰም ያለው አርቲስት አኒስ ገቢ፣ ልጆቻችን የሙዚቃን የትምህርት እድል እንዲያገኙ መንገድ ለማሳየት ነው ወስኜ ወደዚህ ሙያ የገባሁት ብሏል።

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ፣ በአንድ ቃል እና በአንድ ማይክሮፎን፣ አላችሁ ወይ? በማለት ብቻ መላውን ህዝብ አንቀሳቅሶ አለን! በማስባል የሙዚቃ አርት ያለውን ታላቅ ጉልበት አሳይቶናል ብሏል ሙዚቀኛ እና አቀንቃኝ አኒስ ገቢ በቆይታው።

አሰላ ከተማ ውስጥ እንደተወለደ የሚናገረው አርቲስቱ ስለግል ህይወቱ ሲናገር እኔ ስወለድ አባቴ በማረሚያ ቤት ውስጥ ስለነበር፣ አባቱ ባይኖርም እሱን መወከል ይችላል ብለው፣ አኒስ ገቢ ብለው ስያሜ አወጡልኝ ብሏል።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዳማ እና በአሰላ ከተማ መከታተሉን ገልጾ፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ደግሞ ወሎ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በሙዚቃ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

የኦሮምኛ ሙዚቃ ሬዲዮ ይሰብራል ተብሎ ይገለልበት ከነበረው ደረጃ አልፎ ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቀሰው አርቲስት አኒስ፣ አንጋፋዎቹ ለህዝቡ በሥነ ጥበቡ በኩል በር የከፈቱ የኦሮሞ አርቲስቶች ተቸግረው እና የአልጋ ቁራኛ በሚሆኑበት ሰዓት የሚታከሙበት ገንዘብ አጥተው የሚሞቱ ብዙ መሆናቸውን ገልጿል።

የኦሮምኛ ሙዚቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል ብሎም ሙዚቃውን ለማሳደግ አርቲስቶች በትምህርት እና በስልጠና ሊታገዙ እንደሚገባ አርቲስት አኒስ ገቢ ጥሪውን አቅርቧል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review