AMN- ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ የፖለቲካ መዲናም ናት። ተጓዡ የዶክመንታሪ አዘጋጅና ተራኪ ኢብራሂም ጋኖ፣ “አዲስ አበባ ታሪክን በልቧ ይዛ፣ ዘመናዊነትን በእጆቿ እያነሳች ዛሬ ፍጹም አዲስ ገፅታ ተላብሳ ብቅ ብላለች” ሲል ገልጿታል።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከተማዋ የመንገዶቿን መልክ በመቀየር፣ የእግረኞችና የብስክሌት መንገዶችን በማስፋት፣ የልጆች መጫወቻ ስፍራዎችን በመፍጠር እና አረንጓዴ የተላበሱ መናፈሻዎችን በማስዋብ የከተማ መዘመን ምሳሌ መሆኗንም ያነሳል።

የኤሌክትሪክ ባቡር ትራንስፖርትን ቀደም ብላ ወደ አገልግሎት ማስገባቷ አዲስ አበባን ወደ ሽግግር ያመራት ዋነኛ መነሻ ነበር። ይህ ልማት ከተማዋን ብቻ ሳይሆን፣ የነዋሪዎቿን የኑሮ ዘይቤም ቀይሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ሲመጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች በአደባባይ ወጥተው ያሳዩት ድጋፍ፣ ኢትዮጵያ የለውጥ መንፈስ እንዳላት አመላካች እንደነበር ይገልፃል። ከዚያም በኋላ ከተማዋን ለማበልጸግ በርካታ የልማት ተልዕኮዎች ተጀምረዋል።

በከተማዋ ውስጥ እየተገነቡ ያሉ ረጃጅም ህንፃዎች፣ ቅንጡ አፓርታማዎች እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን እያበረታቱ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ሀብታም ግለሰቦች፣ ኩባንያዎች እና ተቋማት ቢሊዮን ዶላሮችን ኢንቨስት አድርገዋል ሲል ተናግሯል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር የባህር በር የሌላት ትልቋ ሀገር ናት። የህዝብ ቁጥሯ እያደገ መምጣትና የኢኮኖሚ ፍላጎቷ መጨመር የባህር በር ጥያቄን ወደ ፊት አምጥቶታል።
በተመሳሳይ ጊዜ 6 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችለውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሷ ወጪ መገንባቷ የሀገሪቱን አቅም አሳይቷል ሲል ተጓዡ የዶክመንታሪ አዘጋጅና ተራኪ ኢብራሂም ጋኖ ይናራል፡፡
ዛሬ አዲስ አበባ በታሪክና በዘመናዊነት መካከል የተመጣጠነ መንገድ እየመረጠች ያለች ከተማ ናት፤ የአፍሪካ መዲና ብቻ ሳትሆን የለውጥ ምልክትም ናት።
በታምራት ቢሻው