አዲሱ የሕይወት ምዕራፍ

You are currently viewing አዲሱ የሕይወት ምዕራፍ

ስልጠናው ከሰውበታች እንደሆንኩ ይሰማኝ የነበረውን ስሜት ቀይሮልኛል

የ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ተጠቃሚ ወጣት እሌኒ ውድነህ

ወጣት ሳራ አዱኛ አብዛኛውን የልጅነት እድሜዋን በብዙ መከራና ውጣ ውረድ ማሳለፏን ትናገራለች፤ ቤተሰቦቿ የልጆቻቸውን የዕለት ጉርስ ለማሟላት እንኳን በእጅጉ የሚቸገሩ፣ ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉ መሰረታዊ ፍላጎቶች አንዱ የሆነውን መጠለያ በቅጡ ያላሟሉ፣ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እየተዘዋወሩ ሸራ ወጥረው በሚቀልሱት ጎጆ የሚኖሩ ችግረኞች ሆነው ለበርካታ ዓመታት መኖራቸውን ታስታውሳለች፡፡

ኑሮ በእነ ሳራ ቤት በእጅጉ የከበደና ከእጅ ወደ አፍ ከሚባለው ደረጃ እንኳን ያነሰ ነበር፡፡ ለቤተሰቦቿ የመጀመሪያ ልጅ የሆነችው ሳራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተከታትላለች፤ የቀንስራ ሰርተው ቤተሰቡን የሚያስተዳድሩት አባቷ ድንገት ለህልፈት መዳረጋቸው ለእርሷ ብቻ ሳይሆን በቤተሰቡ ዘንድ ያልተጠበቀ አስደንጋጭና መጥፎ አጋጣሚን አስከተለ፡፡ ይህም ቤተሰቦቿን የማስተዳደር ኃላፊነትን መሸከም ነው፡፡ ሳራ በቀጥታ በጉልበት ስራ ተሰማራች፡፡ ያም ሆኖ የጠበቀችውን ያህል የቤተሰቡን ፍላጎት ለመሸፈን አልሞላ ሲላት ሃያ ዓመት እንኳን ሳትደፍን በወጣትነት እድሜዋ ለስደት ተዳረገች፡፡

ከበርካታ ውጣ ውረድ በኋላ ምንም ጥሪት ሳትቋጥር ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች፤ በወቅቱ እዚህም የረባ ስራ ባለማግኘቷ ኑሮ ገፍትሮ ወደ ጎዳና ህይወት አስገባት፤ በሂደት ሱስ እና ሌሎች አልባሌ ድርጊቶች ውስጥ ገባች። ከለውጡ ወዲህ ለተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች የተጋለጡ ሴቶችን ህይወት ለመታደግ በተደረገ ጥረት ተጠቃሚ ሆና አሁን ህይወቷ እየተሻሻለ መሆኑን ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች። በካዛንቺስ ‘ሴቶች አደባባይ’ አካባቢ የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው እንስቶች መካከልም አንዷ ሆናለች፡፡

ለወጣት ሳራ እና ሌሎች መሠል ችግር ውስጥ ለነበሩ እንስቶች ህይወት መቃናት መሠረት የጣለው፣ ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ነው፡፡ ማዕከሉ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ53 ሺህ 700 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የሕንጻ ብሎኮችን፣ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ፣ ግዙፍ ኤል ኢ ዲ ስክሪን የተገጠመለት የመዝናኛ አምፊቲአትር፤ 4 ነጥብ 1 ሄክታር በላይ ስፋት ላይ ያረፈ የአትክልት እርሻ ማሳ እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው የራሱ የከርሰ ምድር ውሃ ያካተተ ራሱን ችሎ መንደር ተብሎ ሊጠራ የሚችል ግዙፍ ማዕከል ነው፡፡

ማዕከሉ ለተለያዩ ማህበራዊ ቀውስ የተጋለጡ ሴቶችን ተቀብሎ ሁሉን አቀፍ መሠረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦ ከሶስት እስከ ስድስት ወራት የሚቆይ ሙያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ድጋፍና ስልጠናዎችን በመስጠት ለሥር-ነቀል ለውጥ ለማብቃት ታስቦ ነው የተመሰረተው፡፡ ማዕከሉ የሥነ-ውበት፣ የሞግዚትነት፣ የመስተንግዶ፣ የኤሌክትሪክና የሸክላ እንዲሁም የእንጨት ሥራዎች፣ የጋርመንት ስልጠናዎች እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል። ብዙዎችን አስመርቆ ወደ ስራው ዓለም አስገብቷል፡፡

ወጣት ሳራ ከእነዚህ እንስቶች መካከል አንዷ ነች፡፡ በማዕከሉ ቆይታዋ በልብስ ስፌት፣ ሹራብና ጥልፍ ስራ ሰልጥና አሁን በካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ግንባታ ውስጥ በተዘጋጁ ሱቆች ውስጥ ትሰራለች፡፡ ወጣት ሳራ ለስድሰት ወራት በማዕከሉ የወሰደችው ስልጠና ከአስቸጋሪ የህይወት መስመር አውጥቶ ዛሬ ላይ በተቃና መንገድ ህይወቷን ለመምራት አስችሏታል፡፡ ከመሰል ጓደኞቿ ጋር በሰለጠነችበት ሙያ ተደራጅታ በሙሉ ፍላጎትና ተነሳሽነት እየሰራች እንደሆነ ትናገራለች፤ ይህም ለነገ ማንነቷ ትልቅ መሰረት እንደሚሆናት ትልቅ ተስፋ አሳድሮባታል፡፡ ማዕከሉ በፈጠረላት የስራ እድል በምታገኘው ልምድና ክህሎት ነገ የራሷን ድርጅት ከፍቶ የመስራት ትልቅ ህልም እንዳላት ስትናገርም በልበ ሙሉነት ነው፡፡

የ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች ታሪክ የጽናትና የድል ታሪክ ነው ቢባል የተጋነነ አይደለም የምትለው ወጣት እሌኒ ውድነህ ናት፡፡ ወጣት እሌኒ ልክ እንደ ወጣት ሳራ ሁሉ ከ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የህይወት ክህሎት እና የሙያ ስልጠና አግኝታ በተለምዶ ካዛንቺስ ‘የሴቶች አደባባይ’ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የስራ እድል የተፈጠረላት ሴት ናት። “ስልጠናው ከሰው በታች እንደሆንኩ ይሰማኝ የነበረውን ስሜት ቀይሮልኛል። እኔም መስራት እችላለሁ፤ እኔም ለሀገሬ ጠቃሚ ነኝ የሚል መንፈስ እንዲያድርብኝ አስችሎኛል” ብላለች፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሴቶችን ኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግና መብቶቻቸውን ለማስከበር ጠንካራ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የማህበራዊ ሳይንስ ምሑር ብስራት አስፋው (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ ባለሙያው ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በከተማዋ የተገነቡት ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል እና ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራ በድህነት ቅነሳና ማህበረሰባዊ ግንባታ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ድህነት አዋራጅ ነው ያሉት ምሑሩ፣ “ድህነት ሰዎች አካላቸውን እስከ መሸጥ ለሚደርስ ውርደት እንዲጋለጡ ያስገድዳል፡፡ የ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ተጠቃሚዎች ደግሞ በአብዛኛው በዚያ አይነት ሁኔታ ውስጥ ያለፉ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከማዕከሉ ያገኙት ስልጠናና አዲስ የህይወት ምዕራፍ በድህነት ቅነሳ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፤ ድህነት ሲቀንስ ደግሞ ማህበረሰባዊ ክብር ይጎለብታል። ይህም ለሀገር ዕድገት በጎ አስተዋፅኦ ያደርጋል” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የማህበራዊ ሳይንስ ምሑሩ ብስራት (ዶ/ር) ሴቶችን በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ማብቃት ሀገርን እንደማብቃት ይቆጠራል ብለው፣ መንግስትና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ልዩ ልዩ ኢ-ፍትሐዊ ድርጊቶችና አሰራሮችን መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማጎልበትና የስራ አጥነት ችግርን ከመቅረፍ አኳያ የተጀመሩ ስራዎች መጠናከር አለባቸው። በተለይም በክህሎት፣ በፋይናንስ፣ በመስሪያ ቦታና በገበያ ትስስር ረገድ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች ደረጃ በደረጃ ለማቃለል የሚያስችሉ የግንዛቤና ንቅናቄ ስራዎችን በስፋት መሥራት ይኖርባቸዋል ሲሉ መክረዋል፡፡ እንደ ከተማ በጥቃቅን ንግድ ላይ በተለይ በ‘ለነገዋ’ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በልብስ ስፌት፣ በሹራብ ስራ እና በሌሎች የእደ ጥበብ ስራዎች ሰልጥነው ወደ ስራ የተሠማሩ ሴቶች በተለያየ መንገድ ድጋፍና የገበያ እድል እንዲያገኙ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡባቸው ኤግዚብሽንና በዛሮች እንዲመቻችላቸው መደረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ከ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ባገኘነው መረጃ መሰረት፣ ማዕከሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ሴቶች ወደ ማህበረሰቡ በብቃት እንዲቀላቀሉ ከማድረግ አኳያ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አድርጓል። በዘመናዊ መልክ የተደራጁ የስልጠና ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ በእነዚህም የእድሉ ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች ልብስ ስፌትና ዲዛይን፣ የባህልና ዘመናዊ ልብሶችን የመስፋት ጥበብን ይቀስማሉ። የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ምግቦች አሰራር፣ የፀጉር ስራና ውበት አጠባበቅ ስራዎች ስልጠና ይሰጣል። ማዕከሉ የሙያና የህይወት ክህሎት ስልጠና ከመስጠት ባሻገር ለሰልጣኞቹ መጠለያ፣ ምግብ፣ የህክምና አገልግሎት እና ለልጆቻቸው የቀን ውሎ ማቆያ በማዘጋጀትም ሁለንተናዊ ድጋፍ ያደርጋል። ይህም ሴቶቹ ያለ ስጋት በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ይረዳቸዋል።

የተቋሙ አገልግሎት በዚህ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ሴቶቹ የስልጠና ጊዜያቸውን አጠናቅቀው በሰለጠኑበት ዘርፍ የስራ እድል ከተመቻቸላቸው በኋላም ከገበያ ጋር እንደሚያገናኝም ነው ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ የሚያመላክተው፡፡ እንደ መረጃው ተቋሙ ስልጠናውን ያጠናቀቁ ሴቶች የስራ እድል እንዲያገኙ ከግል ድርጅቶች ጋር ስምምነት ያደርጋል። በተጨማሪም የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት የመስሪያ ቦታና የመነሻ ካፒታል እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። በካዛንቺስ አካባቢ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ብቻም ሳይሆኑ ሌሎችም በልብስ ስፌት የሰለጠኑ ሴቶች አሁን የራሳቸውን ሱቅ ከፍተው ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ አሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በትልልቅ ሆቴሎች ውስጥ በምግብ ዝግጅት ስራ ተቀጥረው በማገልገል የተረጋጋ ህይወት እየመሩ ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም በጎዳና ላይ ልጆቻቸውን ይዘው ይሰቃዩ የነበሩ እናቶች፣ ዛሬ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ልከው ማታ በሰላም የሚገቡበት ቤት እንዲኖራቸው ማዕከሉ መሰረት ሆኗቸዋል። ይህንን በካዛንቺስ ተገኝተን ያነጋገርናቸው እናቶችም ይመሰክራሉ፡፡ ተቋሙ ሴቶችን በክህሎትና በስነ-ልቦና በማነፅ፣ ድህነትንና ማህበራዊ መገለልን ለመዋጋት ትልቅ አቅም መሆኑን በተግባር አሳይቷል። ይህ ተቋም ይበልጥ እንዲጠናከርና መሰል ማዕከላት እንዲስፋፉ ማድረግ፣ በችግር ውስጥ ያሉ ብዙ ወገኖችን ማዳን ነውና የሁሉንም ትኩረት ይሻል፡፡

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review