በአዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም ይኸው የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ከተሰናዱ ዋና ዋና ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የመጽሐፍ ምርቃት፣ የንባብ ውይይት፣ የሥዕል አውደርዕይ እና የቴአትር መርሃ-ግብር ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የተወሰኑትን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
የንባብ ፌስቲቫል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ለ13ኛ ጊዜ የንባብ ሳምንት አዘጋጅቷል፡፡ የንባብ ፌስቲቫሉ “ንባብ ለላዕላይ መዋቅር ለውጥ” በሚል መሪ ሀሳብ በከተማ ደረጃ ከታኅሣሥ 16 እስከ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት ተከታታይ 5 ቀናት ካዛንቺስ በሚገኘው የህዝብ መዝናኛ (ወተር ፓርክ) እየተካሄደ ነው። ፌስቲቫሉ የተዘጋጀው የትውልዱን የንባብ ባህል በማጎልበት ብቁ ዜጋ ለመፍጠር፤ የህብረተሰቡን መስተጋብር ለማጎልበት፤ የሥነ-ጽሑፍ እና የፈጠራ ስራን ለማሳደግ፤ መጻሕፍት ቤቶችን እና ደራሲያንን ለማበረታታት፣ ከአንባብያን ጋር የሚገናኙበትን አውድ ለመፍጠር በተጨማሪም የመጽሐፍት ሻጮች በሥራቸው እንዲጠናከሩ መነቃቃትን ለመፍጠር ታስቦ እንደሆነ ተነግሯል። ከንባብ ፌስቲቫሉ ጎን ለጎን በዘርፉ ምሁራን ተዘጋጅቶ የሚቀርብ የፓናል ውይይት (ቶክሾው) እንደሚካሄድም ቢሮው አስታውቋል፡፡
መጽሐፍት በዛሬው እለት “ጊዜን መሸከም” የተሰኘው የግጥም መጽሐፍ ተመርቆ ለንባብ ይበቃል፡፡ የገጣሚ ዘውዴ አለልኝ የግጥም ስብስቦችን የያዘው ይህ መጽሐፍ ከለም ሆቴል ወደ ኢምፔሪያል ጥቂት መቶ ሜትሮች ገባ ብሎ በሚገኘው በመሶብ የባህል ሙዚቃ ማዕከል ተመርቆ ከአንባቢያን እጅ ይደርሳል፡፡ የመጽሐፍ ምረቃ መርሃ-ግብር ከ10 ሰዓት ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን ወጣት ገጣሚያን እና ሐያሲያን እንደሚታደሙ ተገልጿል፡፡
በሌላ መረጃ የራስ ሳባ ሲሳይ የግጥም መድብል ለንባብ በቅቷል፡፡ “የብርሃን ጥሞና” የተሰኘው ይህ መጽሐፍ የብርሃንን ውበት፣ የብርሃንን ሙቀት፣ የብርሃንን ህይወትነት፣ የብርሃንን እምነት እና ጥበብነት የሚያሳይ ነው ተብሏል። ደራሲዋ በተለያዩ ጋዜጣዎች እና ሬድዮ ጣቢያዎች የግጥም ስራዎችን በመቅረብ የምትታወቅ ሲሆን አሁን ደግሞ የመጀመሪያ የሆነችውን “የብርሃን ጥሞና” የተሰኘ የግጥም መጽሐፍ ለንባብ አብቅታለች፡፡
የስዕል አውደርዕይ “የራስ መንገድ” የተሰኘው የስዕል አውደርዕይ በእይታ ላይ ይገኛል። በዮሴፍ ሰቦቅሳ (ሰናይት) የቀረበው ይህ የስዕል አውደርዕይ ከቀናት በፊት ለእይታ መብቃቱ የሚታወስ ነው፡፡ አውደርዕዩ እስከ ታህሳስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በእይታ ላይ እንደሚቆይም ተገልጿል። የስዕል አውደርዕዩ እየታየ የሚገኘው መስቀል አደባባይ አጠገብ በሚገኘው በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ፈንደቃ የባህል ማዕከል ውስጥ ነው፡፡
ፊልም አቀንቃኙ (ዘ ሲንገር) የተሰኘ አዲስ ፊልም ለእይታ ሊበቃ ነው፡፡ ፊልሙ የተሰራው በተስፋጽዮን መኩሪያ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ በፊልሙ ታዋቂና አዳዲስ ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡ ከእነዚህም መካከል ሰይፈሚካኤል ተስፋዬ፣ ፍሬህይወት ታምራት፣ ሙሉአለም ጌታቸው፣ ኤፍሬም ታደሰ፣ ሳሙኤል ተስፋዬ፣ ቲና ገብረአምላክ፣ መስከረም አማረ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ፊልሙ በቅርቡ ተመርቆ ለእይታ እንደሚበቃ ተገልጿል፡፡
የቴአትር መርሃ-ግብር በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በተለያዩ ቀናት የተለያዩ ቴአትሮች ለጥበብ አፍቃሪያን የሚቀርቡ ይሆናል፡፡ እነዚህም ቅዳሜ ቀን 8፡30 ሰዓት ላይ 12ቱ እንግዶች እንዲሁም 11፡30 ሰዓት ባሎችና ሚስቶች ለእይታ ይበቃሉ፡፡ እሁድ በ8፡30 ሰዓት ንጉሥ አርማህ ቴአትር፣ በ11፡30 እምዩ ብረቷም እንዲሁ ለተመልካች ይቀርባሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማክሰኞ 11፡30 ሰዓት ሶስቱ አይጦች፣ ረቡዕ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ፣ ሐሙስ በ11፡30 ሰዓት ሸምጋይ እንዲሁም አርብ በተመሳሳይ ሰዓት ዴጊያ የተሰኙ ቴአትሮች ከሚታዩት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ከቀናት በፊት የተመረቀው “የመጨረሻው ፍርድ” የተሰኘ ቴአትር ደግሞ ዘወትር እሁድ ከቀኑ 11:30 እስከ ምሽቱ 1:30 በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለእይታ እንደሚበቃ ተገልጿል፡፡
በጊዜው አማረ