የሰባ ደረጃ ፍካት

You are currently viewing የሰባ ደረጃ ፍካት

አንዳንድ ሥፍራዎች ስማቸው ከትውልድ ትውልድ ሳይደበዝዙ ይዘልቃሉ፡፡ በጊዜ ጅረት ውስጥ እየፈሰሱም ዋናኛ መገለጫቸውን ሳይለቁ ዘመን ይሻገራሉ፡፡ የትናንቱን ከዛሬው ጋር በማስተሳሰር ትውስታን ይቀርጻሉ፡፡ ህይወት ዘርተው ትዝታን ያፈራሉ፡፡

ልክ እንደ ‘ሰባ ደረጃ’ ያሉ ሥፍራዎች ትናንትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ ጋር በማሰናኘት የዝመና ሂደት አብነት ይሆናሉ፡፡ በአዲስ መልክ የተሰራው ሰባ ደረጃም ይህንኑ ነው የሚመሰክረው፡፡ በእርግጥ ሰባ ደረጃ የስሙና የታሪኩን ያህል ውብ አልነበረም፡፡ በጥበብ ሥራዎች የተደነቀውን ያህል፣ በአካል ሲያዩት ስሙን ከተግባሩ ጋር ማሰናኘት ተስኖት ደብዝዞ ነበር፡፡ አንዱ ምክንያት ትውልድ ሄዶ በመጣ ቁጥር ይሄ ነው የሚባል ማሻሻያ ሳይደረግለት እዚህ ዘመን ላይ መድረሱ ነበር፡፡ ውበቱም ሆነ ቀለሙ እንደደበዘዘ አልፎ ሂያጁን ሲታዘብ ለዘመናት ኖሯል፡፡ የማታ ማታ ግን ሰባ ደረጃ ስሙን ከግብሩ ጋር ያሰናኘ ለውጥ አድርጓል፡፡

አሁን ሰባ ደረጃ ያ የደበዘዘው መልኩ ተቀይሯል፡፡ ስሙን ብቻ ሳይሆን ግብሩም ገዝፏል፡፡ አቧራ ጠጥተው የነበሩት የደረጃዎቹ ጡቦች በአዲስ መልክ ተቀይረዋል፡፡ መውጫ መውረጃዎቹም በአበቦች ተጊጠዋል፡፡ ጠባብ የነበረው ሰባ ደረጃ ወደ ጎን ሰፍቶ ጥሩ የመዝናኛ ሥፍራ ሆኗል፡፡ ይኸው! ታሪኩንና ስሙን በሚመጥን ደረጃ ተሰርቶ የሕዝቡ ማረፊያ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም ሰባ ደረጃን አመሻሽ ላይ የጎበኘ ሲሆን፣ በስፍራው የነበሩ ግለሰቦችን አነጋግሮ ቀጣዩን መጣጥፍ አጠናቅሯል፡፡

ሰባ ደረጃ ትናንትና ዛሬ

ባለፈው ሳምንት ረዕቡ ሰባ ደረጃን ተዘዋውሬ ለመጎብኘት 12፡00 ሰዓት ገደማ ወደ ሥፍራው ለማቅናት ጉዞዬን ጀመርኩ፡፡ የንፋሱ ሽውታ በጆሮዬ ሽውው… ብሎ እያለፈ ከአራት ኪሎ ቀኜን ይኜ እየተጓዝኩ ነው፡፡ በአጠገቤ ሥራ ውለው ወደ ቤት ለመጓዝ ፈጠን ፈጠን እያሉ የሚራመዱ አዲስ አበቤዎችን እየቃኘሁ፣ የአርመን ኦርቶዶክስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ጋር ደረስኩ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ታሪካዊው ቤተክርስቲያን በግልጽ ስለሚታይ፣ ለአካባቢው ተጨማሪ ግርማ ሞገስ ሰጥቶታል፡፡ በቤተክርስቲያኑ ደጃፍ ላይ የተተከሉት አረንጓዴ ጽዶችን እየቃኘሁ ወደ ነጩ ህንጻ አለፍኩ፡፡

የሰባ ደረጃ ሌላኛው ገጽ

ሰባ ደረጃ የቀደመ ገጽታውን ሳይለቅ ዘምኗል፡፡ መውጫ መውረጃው ጠባብ የነበረው ሰባ ደረጃ ወደ ጎን ሰፍቷል። በብርሃንና በአበባ ተሽቆጥቁጦ ውበት ላይ ውበት ደርቧል፡፡ ከነጩ ህንጻ ሥር ያለው ካፌ በስተቀኝ በረንዳ ላይ ቡና የሚጠጣው ወጣት አጠገብ ቁጭ ብዬ ቡና አዘዝኩ፡፡ ወጣቱ ልጅ የሆነ ነገር ላወራው እንደፈለኩ ገብቶታል፡፡ ራሴን አስተዋውቄው ጨዋታ ጀመርን። እሱ ባለው አወቀ ይባላል፡፡ ዕድሜው በግምት ሰላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ይሆናል፡፡ የሚኖረው ደግሞ ሽሮ ሜዳ ነው፡፡ እሱ ባለው ሥራ ከጨረሰ በኋላ ብዙ ጊዜ በእግር መንሸራሸር ይወዳል፡፡ ከሚሰራበት በተለምዶ ጊዮርጊስ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ በእግሩ እንደመጣና እግረ መንገዱን እዚህ ጎራ እንዳለ አጫወተኝ፡፡

“ሰባ ደረጃን እንዴት አገኘኸው?” አልኩት፡፡ “በጣም አስገራሚ ለውጥ ነው የተደረገለት፡፡ የትናንትና ገጽታውን ሳይለቅ በዚህ ልክ ውብ ተደርጎ መሰራቱ አስገርሞኛል፡፡ እንደምታየው ሰባ ደረጃ ደንበኛ የማረፊያና የመዝናኛ ሥፍራ ሆኗል” በማለት፤ ፊቱን ወደ ቀኝ አዙሮ ሰባ ደረጃን በጉንጮቹ እያመለከተ ስለዛሬው ሰባ ደረጃ ለውጥ አወጋኝ፡፡

እሱ ባለው ሰባ ደረጃ ከመሰራቱ በፊት አልፎ አልፎ ይመጣ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰባ ደረጃ ስሙ ግዝፈት ቢኖረውም፣ ለመቀጣጠሪያና ለመተላለፊያ እንጂ ማረፊያ አልነበረም ሲል አጫውቶኛል፡፡ እሱ ባለውን ተሰናብቼው የሰባ ደረጃን ጡቦች እየቆጠርኩ ወደ ላይ መውጣት ጀመርኩ፡፡ ትንሽ ደረጃውን እንደወጣሁ፣ ዕድሜያቸው በግምት ሰላሳዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኙ ጥንዶች ትኩረቴን ሳቡት፡፡ ደረጃው ላይ ቁጭ ብለው ያወጋሉ፡፡ ‘ሄጄ ላውራቸው ወይስ ልለፋቸው…’ እያልኩ ለሴኮንድ እያመነታሁ ቆየሁ፡፡ ‘ግድ የለም’ ብዬ ቀረብ በማለት ‘ሰላም!’ አልኳቸው፡፡

ወንዱ ቀና ብሎ በስሱ ፈገግ በማለት ‘ሰላም!’ አለኝ፡፡ ራሴን አስተዋውቄ ከአጠገባቸው ቁጭ አልኩኝ፡፡ ባልና ሚስት ናቸው፡፡ ወንዱ ሰለሞን ሃይሉ፣ ሴቷ ቤተልሄም ጣሰው ትባላለች፡፡ “ፍቅራችሁን የሮሚዮና ጁልዬት ያድርግላችሁ!” አልኳቸው፡፡ “የበዛብህና የሰብለወንጌል ቢሆን አይሻልም?” ሰለሞን ፈገግ ብሎ ተመለከተኝ፡፡ “ትክክል ብለሃል፡፡ አሜን! የበዛብህና የሰብለወንጌል ያድርግላችሁ!” ራሴን አርሜ ፈጠን ብዬ ምላሽ ሰጠሁ፡፡

ቤተልሄም በተጠቀለለ ወረቀት ላይ ከያዘችው ቺብስ እንድይዝ ጋበዘችኝ፡፡ ቺብሱን እየቆረጠምኩ፣ “ወንደላጤዎች እዚህ እንዳይቀመጡ ተከልክሏል እንዴ?” ጥያቄዬን በቀልድ አዋዝቼ ጀመርኩ፡፡ ሁለቱም ፈገግ ብለው ተመለከቱኝ፡፡ “ያላገቡ ሰዎች በፍጥነት ያግቡ፡፡ ይኸው ጎዳናዎቹም ፍቅር ይዘምራሉ፡፡ ሰባ ደረጃ እንኳን ከወንደላጤዎቹ ይልቅ ጥንዶችን ኑልኝ ብላ እየተጣራች ነው” ሰለሞን ፈገግ ብሎ መለሰልኝ፡፡ በእርግጥ ፈንጠር ፈንጠር ብለው የተቀመጡት በአብዛኛው ጥንዶች ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ ለብቻቸው የተቀመጡ ጥቂት ወጣቶችም ይታያሉ፡፡

“እንዴት ነው ሰባ ደረጃ?” ሰለሞንን ጠየኩት፡፡ “በጣም አምሮበታል! ግሩም ተደርጎ ነው የተሰራው” እኔና ቤተልሄምን አፈራርቆ እየተመለከተ መለሰልኝ፡፡

ሰለሞን ቀበና ነው ተወልዶ ያደገው። አሁን ላይ ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ ኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ ከሚስቱ ቤተልሄምና ከአንድ ሴት ልጃቸው ጋር ይኖራሉ፡፡ ሰባ ደረጃ የበፊትና የአሁኑ ገጽታው በቀልድ አስመስዬ የግል ትውስታዬን በጨረፍታ አወጋኋቸው፡፡ የእኔን ጨዋታ ተከትሎ፣ ሰለሞን ሰባ ደረጃ ከልጅነቱ አንስቶ እንደሚያውቀው አጫወተኝ፡፡ ያለፈውን ትዝታውን ከአሁኑ የሰባ ደረጃ ገጽታ ጋር እያነጻጸረ ብዙ አወጋን፤

“ሰባ ደረጃን ይበልጥ የማስታውሰው ከጓደኞቼ አመሻሽ ላይ ከቀበና ተነስተን በመምጣት ደረጃው ላይ ቁጭ ብለን አልፎ ሂያጁን እንመለከት ነበር፡፡ በፊት በአብዛኛው ደረጃው መተላለፊያ ድልድይ ሆኖ ነበር የሚያገለግለው፡፡ ከወደ ናዝሬት ትምህርት ቤት የሚመጣውና ከታች ወደ ላይ የሚወጣው የሰው ግርግር ማብቂያ አልነበረውም፡፡ ደረጃው በግራና በቀኝ ያለው ጠበብ ያለ ስለሆነ ለመቀመጥ ብዙም የሚመች አልነበረም። በዚህ ላይ ጥሩ ያልሆነ ሽታ እንደነበረው ትዝ ይለኛል፡፡ ነገር ግን ሰባ ደረጃ ስሙ ታዋቂ ስለሆነ ለመቀጣጠር ምቹ ነበር፡፡ እኔና ጓደኞቼ ሰባ ደረጃ ላይ ቁጭ ብለን ካወጋን በኋላ ፊት ለፊት ወደሚገኘው ትራኮን ሆቴል ጎራ እንል ነበር፡፡ ያን ጊዜ ፑል ቤት ብርቅ ስለነበረ ፑል ለመጫወት ነበር ትራኮን የምንመጣው፡፡

ሌላው ሰባ ደረጃን የማስታውሰው እሁድ ማለዳ ላይ ስፖርተኞች ደረጃውን ወጥተው ሲወርዱ ነው፡፡ ደረጃዎቹ ለስፖርት ምቹ ስለሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይመረጥ ነበር፡፡ ከዚህ ያለፈ ግን ሰባ ደረጃ እንደ መዝናኛ ሥፍራ የሚቆጠር አልነበረም፡፡ አሁን ላይ ግን ሰባ ደረጃን መልሶ ውብ ተደርጎ በዚህ መልኩ በመሰራቱ ለአካባቢው ተጨማሪ የአይን ማረፊያ ለመሆን በቅቷል፡፡ ከሁሉም በላይ አዲስ አበባ እንዲህ አይነት ክፍት የመዝናኛ ሥፍራዎች ያስፈልጓት ነበር፡፡ ታሪካዊው ሰባ ደረጃ ታሪካዊነቱን ሳይለቅ በዚህ መንገድ እንደገና መሰራቱ ይበል የሚያሰኝ ነው!” በማለት ሰለሞን የሰባ ደረጃ ትዝታውን ከዛሬው ጋር እያነጻጸረ አጫውቶናል፡፡

“በፊት ከሰለሞን ጋር እዚህ ሰባ ደረጃ ተቀጣጥራችሁ አታውቁም?” በአትኩሮት ወጋችንን ስትሰማ የነበረችውን ቤተልሄምን ጠየኳት፡፡ አንገቷን ግራና ቀኝ በመነቅነቅ “ተቀጣጥረን አናውቅም” አለችኝ። ሀዋሳ ተወልዳ ያደገችው ቤተልሄም፣ በእግር መንሸራሸር ትወዳለች፡፡ እንደ ሰባ ደረጃ ያሉ ክፍት ሥፍራዎች ላይ ቁጭ ብሎ መዝናናት እንደሚያስደስታት አጫውታኛለች፡፡ ሰባ ደረጃ ከተሰራ በኋላ ሰለሞን ባይኖርም ከልጇ ጋ አመሻሽ ላይ አዘወትራ እንደምትመጣም አክላ አወጋችኝ፡፡

ሰባ ደረጃ ታሪካዊ ከሆኑ የአዲስ አበባ ቀደምት ሥፍራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን ለዓመታት ይሄ ሥፍራ ዓይን ውስጥ የሚገባ ዕድሳት ተደርጎለት አያውቅም ነበር፡፡ ስመ ገናናው ሰባ ደረጃ፣ ስሙን የሚመጥን ቁመና ላይ አልነበረም፡፡ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት አካል በመሆን፣ የተደረገለት ዕድሳትና መልሶ ግንባታ ግን ሰባ ደረጃ ስሙን ከተግባር ጋር እንዲያሰናኝ አስችሎታል፡፡ እኔም የበፊቱን ሰባ ደረጃና እንደገና ተሰርቶ ክፍት የተደረገውን ሰባ ደረጃን በምናቤ እያመላለስኩ በናዝሬት ትምህርት ቤት አልፌ ወደ ቤቴ አቀናሁ፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review