ትውልዱን ከጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችየሚታደገው እርምጃ

You are currently viewing ትውልዱን ከጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችየሚታደገው እርምጃ

የውጭ ባህላዊ ድርጊቶችን እና ክብረ በዓላትን የሚያከብሩ ትምህርት ተቋማት ወይም ግለሰቦች 150 ሺህ ብር እንደሚቀጡ ተገልጿል

“በቅርብ ርቀት ነው፤ አንዳች የሚያስተጋባ ድምፅ ከፊት ለፊቴ ድንገት አቃጨለ፡፡ ድምፁ የብዙ ሰዎች እንደሆነ ገምቻለሁ፡፡ ቆም ብዬ አዳመጥኩ፤ በምሄድበት የአስፓልት መንገድ እየመጡ እንደሆነም አረጋገጥኩ፡፡ ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ ወደፊት ሳማትር ጭቃ የተለቀለቁ ወጣቶችን ተመለከትኩ፡፡ እየተጠጋሁ ስሄድ ማንነታቸውንና የፊታቸውን ገጽታ መለየት ባልችልም በትከሻቸው ባነገቡት ቦርሳ ተማሪዎች እንደሆኑ ገምቻለሁ፡፡

ግምቴ ትክክል ነበር፡፡ ግን የየትኛው ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንደሆኑ ልብሳቸው በቀይ አፈር የተጨማለቀ በመሆኑ ልለያቸው አልቻልኩም፡፡ ከአራት ኪሎ ወደ ስድስት ኪሎ እየተጓዙ ስለነበር የዚያው አካባቢ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንደሚሆኑ ገመትኩ፡፡ ከላይ እስከ ታች ጭቃ መቀባቸው ‘ክሬዚ ዴይ’ (Crazy Day) መሆኑ ነው፡፡”

እኔ የምለው ይህ “ክሬዚ ዴይ፣ ወተር ዴይ፣ ኦልዲስ ዴይ፣ ፒጃማ ዴይ፣ ቫላንታይን ዴይ፣ ቶማቶ ዴይ… እያሉ በምዕራባውያን ባህል ውስጥ ዘው ብሎ መግባትና ግራ ተጋብቶ ሌሎችን ግራ ማጋባት ምን የሚሉት ዘመናዊነት ነው?” የሚለው አንድ ወዳጄ የገጠመውን በአንድ ወቅት በፌስቡክ ገጹ ካጋራው የተጋራሁት ነው፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ወላጅ ይህን ትዝብት የሚያጠናክር አስተያየት እንደሚከተለው አጋርተውኛል፤ “ጫማውን የገዛሁት በወቅቱ ውድ በሚባል ዋጋ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ልጄ የጫማውን ዋጋ እና አቅም ያህል አልተጠቀመችበትም፡፡ ይልቅስ አንድ ቀን ከትምህርት ቤት መልስ ጫማው በውሃ በስብሶ እና በተለይ የአንደኛው እግር ከፊት ለቆ ማድረቅ ባለመቻሏ ከቦርሳዋ በተጨማሪ እሱንም በእጇ ይዛ መጣች፡፡ የለበሰችው ልብስ በውሃ ርሷል፡፡ ጸጉሯም እንደረጠበ ነው፡፡ በንዴት ምክንያቱን ስጠይቃት በትምህርት ቤታቸው ወተር ዴይ (የውሃ ቀን) በመከበሩ እንደሆነ በኩራት ነገረችኝ፡፡”

እኝህ ወላጅ በወቅቱ በአስፈላጊነቱ ላይ ከልጃቸው ጋር ያደረጉት ውይይት መግባባት ላይ ያላደረሳቸው እንደሆነ ነግረውናል፤ በጉዳዩ ላይ ትምህርት ቤት በመሄድ ለመነጋገር ጥረት ቢያደርጉም ተገቢ ምላሽ ሳያገኙ እንደቀሩ ገልጸዋል። በየትምህርት ቤቱ ቀን ተሰጥቷቸው ይከበሩ የነበሩ መጤ ባህሎች ወላጆችን ለኢኮኖሚያዊ ጫና እና ሌሎች ችግሮች፤ ተማሪዎችን ደግሞ የራሳቸውን ባህል በአግባቡ እንዳያውቁ አድርጓቸው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲቀር ማድረጉ ትውልድን መታደግ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን ለመጠበቅ የሀገሪቷን ባህልና ወግ የሚቃረኑ፣ ከባህላችን ጋር የማይሄዱና የመጡበት የማይታወቅ እንደ የእብደት ቀን (Crazy Day)፣ የዋህ ቀን (Gentle Day)፣ የድሮ ቀን (Olds Day)፣ የፍቅረኛሞች ቀን (Valentine Day)፣ የቀለም ቀን (Color Day)፣ የፒጃማ ቀን (Pyjama Day)፣ የትምህርት ማጠናቀቂያ ዝግጅት በተለይ 12ኛ ክፍሎች ከሀገር አቀፍ ፈተና በኋላ የሚዘጋጁት ፕሮግራም (When I Grow Up Party…) እና የመሳሰሉትን የውጭ ባህላዊ ድርጊቶች ማክበር ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑን የሚገልጽ ደንብ ስለመዘጋጀቱ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በዚህ ደንብ ከላይ የተዘረዘሩትን ጨምሮ የውጭ ባህላዊ ድርጊቶች የሚያከብሩ የትምህርት ተቋማት ወይም ግለሰቦች 150,000 (መቶ ሃምሳ ሺህ) ብር ቅጣት እንደሚቀጡ ተገልጿል። በመመሪያው መብትና ግዴታዎች የተቀመጡ ሲሆን፤ በተማሪዎች ግዴታ ስር ጸጉርን በአግባቡ መሰራት/ማሳጠር እና ከተፈጥሯዊ ጸጉራቸው ውጪ እንዳይጠቀሙ ተቀምጧል። የሴቶች የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ ቀሚስ ቁመት ከባት በታች መሆን ያለበት ሲሆን ከአካባቢው ባህል ጋር የማይቃረን ልብስ መልበስ የሚለውም ተካትቷል።

ከተከለከሉት ተግባራት መካከልም ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጣት፣ ጫት መቃም፣ ዕፆችን መጠቀም/ማዘዋወር እንደዚሁም ሞባይልና የሙዚቃ ማዳመጫዎችን ወደ ትምህርት ቤት ይዞ መምጣት ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪም በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ኃይማኖታዊ አምልኮ ስርዓትና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን፣ ሰውነትን መነቀስ፤ ሴት ተማሪዎች የጥፍር፣ የፀጉርና የከንፈር ቀለም መቀባትና መኳኳል እንደዚሁም አላስፈላጊ ጌጥ ማድረግን ይከለክላል።

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም ረቂቅ ደንቡ ከያዛቸው በተለይም የውጭ ባህላዊ ድርጊቶች ትውልድ ግንባታ ላይ ስላላቸው አሉታዊ ተፅዕኖ የሚመለከታቸውን አካላት አናግሯል፡፡ ተማሪ ክርስቲና ነጋሽ የዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ እና የወተመ (የወላጅ፣ ተማሪ እና መምህራን) አባልና የተማሪዎች ተወካይ ነች፡፡ “የውጭ ባህላዊ ድርጊቶች ለእኛ ለተማሪዎች ምንም ጥቅም የላቸውም፤ ምክንያቱም ቀን አስቀምጠን የምናደርገው ድርጊት በትምህርታችን ውጤታማ እንዳንሆን ከማድረግ ባሻገር የራሳችንን ባህል ትተን የሌሎች አድናቂና ተገዢ አድርጎናል፡፡ ተማሪው ቀናቱን ሲያከብር እንደቀላል ተመልክቷቸውም ይሆናል፡፡ ነገር ግን ስር የሰደደ ችግር የሚያመጣ እና የመማር ማስተማሩን ስራ የሚያስተጓጉል ነው” ስትል ገልጻልናለች፡፡

“ባህሎቹን የሚከተሉ ራሳቸውን እንደ ስልጡን ይቆጥራሉ፡፡ ባህሉ ወደ ሀገራችን ለምን እንደገባ ባልተረዳነው ሁኔታ ይህን ተግባራዊ ማድረግ እራስን አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ማንነትን መርሳት ነው” በማለትም አክላለች፡፡ “በትምህርት ቤታችን የሰንደቅ ዓላማ ቀን፣ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን፣ የሰራተኞች ቀንን… እናከብራለን፡፡ እነዚህ ቀናት ትርጉም ያላቸው ናቸው። በመሆኑም እኛ ተማሪዎች በእነዚህ ቀናት አማካኝነት ስለማንነታችን እና ሀገራዊ ክብራችን ለማወቅ ያስችለናል፡፡ እራስንም ሆነ ሀገርን የሚያሳድገው ደግሞ የራስ የሆነ ባህል ነው” ስትል ሀሳቧን ሰንዝራለች፡፡

አበበ አክመል በትምህርት ቤቱ መምህር እና የወተመ ዋና ፀሐፊ ናቸው። እንደሳቸው ገለፃ፤ የውጭ ባህላዊ ድርጊቶች ከመማር ማስተማሩ ባሻገር ትውልዱ ላይ የሚፈጥሩት አሉታዊ ተፅዕኖ በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በዚሁ ትምህርት ቤት እንደሆነ ገልጸው፤ በወቅቱ እነዚህ የውጭ ባህላዊ ድርጊቶች እንዳልነበሩና የሆነ ወቅት እንደ ስልጡን እራስን በማየት የማክበር ሁኔታ እንደመጣ ይናገራሉ፡፡

“እንደ አጋጣሚ ሆኖ ለሥራ ጉዳይ አንዳንድ ሀገሮች ሄጃለሁ፤ አደጉ የምንላቸው ሀገራት ያላቸውን ባህል እና ትውፊት የመጠበቅ ግዴታ ይጣልባቸዋል፤ ምክንያቱም የሀገሪቱ ሀብት ናቸውና፡፡ ለእኛ የሚልኩት ባህል ደግሞ ለእድገትም ሆነ ለለውጥ የማይጠቅም ነው፡፡ እኛም ሳንለይ እንቀበላቸዋለን፡፡ ነገር ግን ዋጋ አስከፍለውናል፡፡ እንደ ሀገር በዓለም ደረጃ የምንኮራበት የቅኝ ግዛት ያለመገዛት ታሪክ አለን፡፡ ያንን ክብራችንን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ያለን ባህልና ትውፊት ትውልዱ በአግባቡ ተረድቶ አለመተግበሩ በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት እየተገዛን ነው፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ በዋናነት ከቤተሰብ ጀምሮ የአካባቢው እና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ፣ በትውልዱ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ በትምህርት ቤታችን ከተማሪዎች፣ ከወላጆች፣ ከመምህራንና ከትምህርት ቤቱ አመራር ጋር እየሰራን እንገኛለን” ሲሉ ሀሳባቸውን አጋርተውናል፡፡

አቶ ስንታየሁ እንድሪስ በትምህርት ቤቱ የወተመ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ የውጭ ባህላዊ ድርጊቶችን በተመለከተ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ “ትውልዱ የተጫነበት ጎጂ የውጭ ባህላዊ ድርጊቶች ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍሉ ናቸው፡፡ ይህ የመጣው ደግሞ አሁን ባለንበት የዲጂታል ዘመን ተፅዕኖ ነው፡፡ የተዘጋጀው ደንብ ለችግሩ መፍትሔ የሚያመጣ ነው” ብለዋል፡፡

የዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ግርማ ነገሬ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ ብሎም እንደ ትምህርት ቤት የውጭ ባህላዊ ድርጊቶች በተለያየ መልኩ ተስፋፍተው ይታዩ ነበር፡፡ ትምህርት ቤታችን ካለበት ቦታ እና ተያያዥ ጉዳዮች አንጻር ችግሩ የሰፋ ነበር፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከሄደበት ርቀት አንዱ የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን መቅጠር ነው፡፡ የባለሙያዎችን ቢሮ በተሟላ ሁኔታ በማደራጀት ተማሪዎች የትምህርት ቤቱን ህግና ደንብ በጠበቀ መልኩ ከአለባበስ ጀምሮ እንዲያከብሩ የማድረግ ስራ ይሰራሉ፡፡ ችግር አለባቸው ተብለው የተለዩ ተማሪዎችን ደግሞ የክትትል እና የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ሌላው በትምህርት ቤቱ የወተመ (ወጣት፣ ተማሪዎች እና መምህራን) አደረጃጀት ነው፡፡ ወተመ ከወላጅ፣ ከተማሪዎች እና ከመምህራን የተዋቀረ እንደመሆኑ ጠንካራ አደረጃጀት እና ለመማር ማስተማሩ ትልቅ እገዛ እያደረገ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡

ርዕሰ መምህሩ አያይዘውም፤ ደንቡ ቀደም ሲል በትምህርት ቢሮ አማካኝነት በተለያየ መልኩ ወርዶ ወደ ተግባር የተገባበት ነው፡፡ ሆኖም በዚህ መንገድ መቅረቡ የጋራ ጉዳይን በጋራ እና በተቀናጀ ለመስራት ያስችላል፡፡ አሁንም ተማሪዎች ላይ የሚስተዋል ያልተገባ ተግባር እንደሚስተዋል ያልሸሸጉት ርዕሰ መምህሩ በተለይ ሀገር አቀፍ ፈተና ለመውሰድ የሚዘጋጁት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የተለየ ፕሮግራም ለማድረግ እና ልብስ ለማሰፋት የሚያደርጉት ሙከራ አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን አስፈላጊነቱ ላይ ከወላጅም ሆነ ከተማሪዎች ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሆነ አያይዘው ነግረውናል፡፡

“ደንቡ የውጭ ባህላዊ ድርጊቶች አላስፈላጊ ከመሆናቸው ባሻገር ለማስተናገድ እድል የሚሰጥ አይደለም” ያሉት ደግሞ በቅድስተ ማርያም ካቶሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ኢዶሳ መርጋ ናቸው፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሦስት በዓላት እንደሚከበር የገለጹት ርዕሰ መምህሩ፤ “አንዱ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ነው፡፡ ተማሪዎቻችን ቀኑን ‘ካልቸር ዴይ’ ብለው ይጠሩት ነበር። የተለያየ ባህል አለ፤ የትኛው ነው? የምዕራባውያን፣ የአፍሪካ ወይስ የኢትዮጵያ? ስለዚህ ቀኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ህገ መንግስታዊ መብታቸው የተከበረበት መሆኑን እንነግራቸዋለን፡፡ ልብሱንም ለብሰው እንዲመጡ እናደርጋለን”፡፡ ሲሉ ካልቸር ዴይ እና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን ለይተው እንዲያውቁ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል፡፡ ሌላው የሰራተኞች ቀን እና የባንዲራ ቀን እንደሆነ ገልጸው በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡

ከትምህርት ቤት ውጪ የሚከበረው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ምርቃት እንደሆነ የሚናገሩት ርዕሰ መምህሩ፣ በዓሉ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ከተፈተኑ በኋላ አንድ ተማሪ ከአንድ ወላጅ ጋር በመገኘት በሸራተን አዲስ ትምህርት ቤቱ በሚያዘጋጀው ፕሮግራም በመገኘት የምርቃት ሥነ ሥርዓት ይካሄድበታል። የሚካሄደው መርሀ ግብር ከትምህርት ቤቱ እና ከወላጅ እውቅና ውጪ አይደለም ሲሉም አክለዋል፡፡ “አንድ ተማሪ ከትምህርቱ በተጨማሪ ብቁ ዜጋ የሚሆነው ከቤተሰብ ጀምሮ በጋራ መስራት ሲቻል ነው” ያሉት ርዕሰ መምህሩ፤ በዋናነት ወላጅ ልጁን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ብቻ ሳይሆን ውሎውንም ሆነ ተያያዥ ጉዳዮችን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ የውጭ ባህላዊ ድርጊቶችን በተመለከተ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ በትምህርት ቤቶች ቀናት ተፈጥረውላቸው የሚከበሩት ስርዓተ ትምህርቱን የሚጎዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ተግባሩ ሲከወን የነበረው የመማር ማስተማር በሚካሄድበት ሰዓት መሆኑ እና ጊዜያቸውን እያባከነ ያለ ሂደት እንደነበር የተናገሩት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ የውጭ ባህላዊ ድርጊቶች የተማሪዎችን ሥነ ምግባር ከማነጽ ሂደት ጋር የማይገናኙ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የውጭ ባህላዊ ድርጊቶች በተማሪዎች ሥነ ምግባር እና በትምህርት ውጤታቸው ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፍባቸዋል፡፡ በተለይም በትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የትምህርት ቤት ንብረት የወደመበት እና ከፍተኛ ጉዳትን ያስከተለ መሆኑ አስቸጋሪ አድርጎት ነበር፡፡ ይህ ነገር እንዳይከሰት መጀመሪያ መደረግ ያለበት ባህርይ ግንባታ ነው፡፡ ተማሪዎች ለእነሱ ጠቃሚ እና ጎጂ የሆኑ ነገሮችን የማሳየት እና የማስገንዘብ ስራ ነው መጀመሪያ መሰራት ያለበት። ይህ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ፤ በተለይ ደግሞ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ እንደሚጎዳቸው የማሳየት ስራ ለተማሪዎች በየትምህርት ቤቶቻቸው ሚኒ ሚዲያን ጨምሮ በተለያዩ ክበቦች አማካኝነት የማሳወቅ፤ በተለይም የውጭ ባህላዊ ድርጊቶች የሚያስከትሉት ጉዳት ምን እንደሆነ የማሳየት፣ እነሱም ይህንን ተረድተው በሂደቱ እንዳይሳተፉ የማድረግ እና የማስገንዘብ ስራ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በየትምህርት ቤቶቹ የሥነ ምግባር፣ ሰላምና ፀጥታ ክበብ አለን፡፡ ትምህርት ቤቶች ላይ በዚህ ክበብ አማካኝነት ተማሪዎች እንዲማሩት እና እንዲያውቁት የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በቀጣይም ትምህርት ቤቶች መጤ ባህሎችን ተግባራዊ እንዳያደርጉት በህግ የመከልከል ስራ ነው የምንሰራው ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ አንዳንዴ በመንግስት ደረጃ የወረዱ ቀናትን ተገን በማድረግ የሚፈልጉትን ነገር ግን ሊተገበሩ የማይገባቸውን የማክበር ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ ያንን የመከልከል ስራ እየተሰራ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ያን ያህል ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቢሮ የሚያስተዳድረው በከተማዋ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን እንደሆነ የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መምህሩ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ወጣ ብሎ ስናገኘው የማስተካከል ስራ እንሰራለን። የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ትምህርት ላይም ትኩረት በመስጠት ተማሪዎች እንዲማማሩ የማድረግ ስራ እንሰራለን። የውጭ ባህላዊ ድርጊቶችንም ሆነ ለመማር ማስተማሩ እንቅፋት የሆነውን ድርጊት ተማሪው እንዲፀየፈው እና ‘የእኔ አይደለም’ እንዲል ደግሞ ግንዛቤውን የማሳደግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን ጨምሮ የተለያዩ ቀናት ሲከበሩ ትምህርት ቢሮ አቅዶ ባወረደው መሰረት ትምህርት ቤቶች እንዲያከብሩት ይደረጋል፡፡ የውጭ ባህላዊ ድርጊቶችን በተመለከተ የተዘጋጀው ደንብም ምንም እንኳን እንደ ትምህርት ቢሮ ቀደም ብሎ ወደ ትምህርት ቤቶች በማውረድ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም የጋራ አፈፃፀም እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ መማር ማስተማሩ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካል እንደመሆኑ የደንቡ አፈፃጸም ላይ ሁሉም ትኩረት ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

በሰውነት ኃ/ጊዮርጊስ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review