ልጆች፤ ስለምትኖሩበት አካባቢ አድራሻምን ያህል ታውቃላችሁ?

You are currently viewing ልጆች፤ ስለምትኖሩበት አካባቢ አድራሻምን ያህል ታውቃላችሁ?

ልጆች፤ እንዴት ናችሁ? በዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን የምትኖሩበትን አድራሻ በማወቃችሁ ምን ትጠቀማላችሁ? ባለማወቃችሁ ምን ችግር ያጋጥማችኋል? የሚሉትን ሃሳቦች እናነሳለን፡፡ ለዚህ ያነጋገርናቸውን ልጆች ልምዳቸውን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡

እያሱ ሲሳይ እባላለሁ፡፡ 12 ዓመቴ ነው፡፡ የምኖረውም ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 መነን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ወደ ትምህርት ቤት የምሄደው ብቻዬን ነው፡፡ በአንድ ወቅት ከእናቴ ጋር ከእኛ ሰፈር ራቅ ወዳለ አካባቢ ሄድን፡፡ ገበያ ነበር፡፡ ከእሷ ጋር ድንገት ተጠፋፋን፡፡ እናቴ እንደነገረችኝ ብትፈልገኝም ልታገኘኝ አልቻለችም፡፡ ስልክ ቁጥሯን ግን በቃሌ አውቀው ነበር፡፡ ሰዎች ደውለው እንዲያገናኙኝ አደረግኩ።

የእናቴን ስልክ ቁጥር ባላውቀው ኖሮ ችግር ሊገጥመኝ ይችል ነበር፡፡ ይህ እንዳይሆን የቤተሰቦቼን ስልክ ቁጥር መያዜ ጠቅሞኛል፤ ጠፍቶ ከመቅረትም ታድጎኛል፡፡ ከቤት በወጣንበት አጋጣሚ የህመም ወይም ሌሎች ችግሮች ሲገጥሙንም ደውሎ ቤተሰብ እንዲወስደን ለማድረግ ይረዳል፡፡ ቤተሰቦቼ ስልክ ቁጥራቸውን እንዳልረሳው ያስጠነቅቁኛል፡፡ “ችግር ከገጠመህ ደውል” ብለው ይመክሩኛል፡፡ እኔም በጥንቃቄ እይዛለሁ፡፡ በዚህም ተጠቅሜበታለሁ፡፡

ዮርዳኖስ ኃይሉ እባላለሁ፡፡ 15 ዓመቴ ነው፤ የምኖረውም ሽሮ ሜዳ ወረዳ 02 ወጣት ማዕከል አካባቢ ነው፡፡ ከትምህርት ቤት ወደ ቤቴ ስመለስ እንዳይጠፋብኝ በሰፈር ባለ ሱቅ፣ የቤት ቀለም እንዲሁም በሰፈሩ ስያሜ ነው አድራሻዬን ለይቼ የማውቀው፡፡ ለችግርና ለተለያዩ ነገሮች የሚደርሱልኝን የቤተሰቦቼን ስልክ ቁጥርም በቃሌ ይዣለሁ፡፡ በትምህርት ቤት ጉብኝት ለመሄድም ይሁን አንዳንድ ቃለመጠይቅ ሲኖር የወላጅ ፍቃድ ስለሚያስፈልግ አድራሻቸውን ነግሬ እንዲደወል አደርጋለሁ፡፡ ከእናትና አባቴ በተጨማሪ የዘመዶቼን ስልክ ቁጥርም እንደ አማራጭ ይዣለሁ፡፡

እየሩስ ዘለቀ እባላለሁ፡፡ ሽሮ ሜዳ አሜሪካን ኤምባሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ነኝ፡፡ 11 ዓመቴ ነው፡፡ ከ7 ዓመቴ ጀምሮ ቤተሰቦቼ ስልክ ቁጥራቸውን ደብተሬ ላይ ይፅፉልኝ ነበር፡፡ ‘ችግር ሲገጥምሽም ስልክ ያለው ሰው ፈልገሽ በዚህ ቁጥር ደውዪልን’ ይሉኝ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የምኖርበትን አድራሻ አውቃለሁ፡፡

አድራሻ ማወቄ ወደምፈልገው ቦታ ለመሄድና ለመመለስ ረድቶኛል፡፡ በሄድኩበት ችግር ቢገጥመኝ እንኳን ቶሎ ደውዬ ወይም ያለሁበትን አድራሻ በመንገር ቤተሰቦቼ እንዲደርሱልኝ አደርጋለሁ፡፡ የምኖርበትንም ሆነ የቤተሰቦቼን ስልክ ቁጥር እንዳውቅ ላደረጉኝ ቤተሰቦቼ አመሰግናለሁ፡፡

ልጆች፤ እናንተም የምትኖሩበትን አድራሻ ማወቅ፣ የቤተሰቦቻችሁን ስልክ ቁጥር መያዝ ለተለያዩ ችግሮች እንዳትጋለጡ ይረዳችኋልና ይኼንኑ መልካም ተግባር ብታደርጉ ጥሩ ነው፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review