ከመታየት ወደ መጠቀሚያነት

You are currently viewing ከመታየት ወደ መጠቀሚያነት

ኮሌጁ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ስራዎችን ሰርቶ ለኢንተርፕራይዞች እያስተላለፈ ነው

ወቅቱ የሰው ልጆችን ድካም የሚያቃልሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እየተሻሻሉ የቀረቡበት ነው፡፡ ዓለማችንም አሁን ላይ የት ደርሳለች? ብለን የጠየቅን እንደሆነ አይናችን ያየውን ጆሯችን የሰማውን ማመን በቂ ይሆናል፡፡ ታድያ ዓለም በዚህ ልክ የተሻሻሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይፋ ስታደርግ፤ ሀገራችንም ለዚህ የቴክኖሎጂ እድገት የሰጠችው ምላሽ ምን ይመስላል? ለሚለው ጥያቄ፤ በተለይ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ያለው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነው የሚል ምላሽ መስጠት በቂ ነው፡፡

ለዚህ አቅም እየሆኑ ካሉ የትምህርት ተቋማት መካከል ተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አንዱ ነው፡፡ ከማስተማር ልምድ ባሻገር በርካቶችን የሙያ ባለቤት ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የአሰልጣኞች ሚና እጅግ የላቀ ነው፡፡ ይህንንም ያለንበት ምክንያት እንደ ተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በመሳሰሉ የማሰልጠኛ ተቋማት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመፍጠር ረገድ እንደ ሀገር እያበረከቱት ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡

በርካቶችን የሙያ ባለቤት ያደረገው ኮሌጁ ለፈጠራ ብሎም ለቴክኖሎጂ ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ፖሊቴክኒክ ኮሌጁ በበርካታ የትምህርት መስኮች ስልጠናዎችን ለተማሪዎቹ ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ችግር ፈቺ፣ ሀገር ከጎደላት ላይ የሚሞላ፣ ትውልድን በማብቃት ረገድ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡

በኮሌጁ የቴክኖሎጂ ዲዛይንና አዋጭነት የማረጋገጥ የስራ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት አቶ አሰፋ ዳኜ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በርካታ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ስራዎች በኮሌጁ እየተሰራ፣ ወደ ኢንተርፕራይዞች የማስተላለፍ ስራም በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንደ አቶ አሰፋ ገለፃ፤ የውስጥ አቅምን በማሳደግ፣ ሀገራዊ ተልዕኮን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት በፖሊቴክኒክ ኮሌጆች የሚሰጡ የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ልምምድ ስልጠናዎች በሀገር ሁለንተናዊ እድገት ላይ አበርክቷቸው እጅግ የላቀ ነው፡፡

በተለይም ለኤግዚቢሽንና ለውድድር ተብለው የሚዘጋጁ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ውጤቶች አቧራቸውን አራግፈው ጥቅም እንዲሰጡ፣ የፈጠራ ባለሙያዎችን ብቃትና ክህሎት እንዲተዋወቁ፣ የውስጥ አቅምን እንዲደግፉ እንዲሁም የኢንተርፕራይዞች ምርታማነታቸው እንዲጨምር ትልቅ አቅም እየፈጠረላቸው ይገኛል፡፡

የተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የቴክኖሎጂ ዲዛይንና አዋጭነት የማረጋገጥ የስራ ክፍል በተለይ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ላይ የዳሰሳ ጥናት ያካሄዳል፡፡ በዚህም ለመስራት የታሰበውን የቴክኖሎጂ ውጤት አዋጭነቱን በመተንተን፣ በኮሌጁ ውስጥ ያሉ የስልጠና ክፍሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶቹን እንዲሰሩ ፍቃድ ይሰጣል፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ በሚፈለገው ልክ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር የሚያስችል ማንኛውንም አገልግሎት በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ያስችል ዘንድ አዋጭ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በኮሌጁ በሚገኙ አሰልጣኞች አማካኝነት ይሰራሉ፡፡ አሰልጣኞች እንደየዘርፋቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተደራሽ በማድረግ የኢንተርፕራይዞችን የምርት መጠን ለማሳደግ እንደሚሰሩ ጭምር አስታውቀዋል፡፡

እስካሁን በፖሊቴክኒክ ኮሌጁ አሰልጣኞች የተሰሩ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎችን በተመለከተ አቶ አሰፋ ሲያስረዱ፤ ከተሰሩት በርካታ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች መካከል፦ የወተት ማርጊያ እና የአፈር ማዳበሪያ ማምረቻ ማሽኖች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የፈጠራ ውጤቶች በኮሌጁ አሰልጣኞች ተሰርተው ለኢንተርፕራይዞች የተሸጋገሩ ናቸው። በተጨማሪም፤ የከተማ ግብርና ዘርፉን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን በመስራት በኮሌጁ ለሚገኙ ዶሮዎችና ላሞች የተመጣጠነ መኖ ለማዘጋጀት ተችሏል፤ በቀጣይም ለኢንተርፕራይዞች የማሸጋገር ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

በኮሌጁ የቴክኖሎጂ ዲዛይንና አዋጭነት የማረጋገጥ የስራ ክፍል አስተባባሪው እንዳስረዱት፤ የተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ችግር ፈቺ የሆነውን የመኖ ማቀነባበሪያ ማምረቻ ማሽን ለመስራት ከየዲፓርትመንቱ የተውጣጡ አሰልጣኞችን በማቀናጀት ወደ ስራ አስገብቷል፡፡ በዚህም መሰረት ምርቱን ለማምረት የተሳተፉ አካላት የብረታብረት፣ የሜካኒክስ፣ የኤሌክትሪካል ኤሌክትሮኒክስ፣ የአውቶ እንዲሁም የከተማ ግብርና የትምህርት ክፍሎች አሰልጣኞች በ2017 ዓ.ም የመኖ ማቀነባበሪያ ማምረቻውን ሰርተውታል፡፡ በፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙ ዶሮዎችና ላሞች በመኖ ማቀነባበሪያ አማካኝነት የተዘጋጀውን መኖ እንደሚጠቀሙ ጭምር አስታውቀዋል፡፡

”የመኖ ማቀነባበሪያ ማምረቻው ከውጭ ሀገር ገዝተን ብናስገባ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ያስወጣን ነበር” ያሉት አቶ አሰፋ፤ ነገር ግን የፈጠራ ስራው በኮሌጁ አሰልጣኞች መሰራት በመቻሉ ቴክኖሎጂውን ለማምረት የፈጀው ገንዘብ 600 ሺህ ብር ብቻ ሊሆን ችሏል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በተግባር ተፈትሾ ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ሲሆን፤ 100 ኩንታል የሚሆን ለመኖ ማቀነባበሪያነት የሚውል ግብዓትን በ30 እና በ40 ደቂቃ ውስጥ አድቅቆ የማውጣት አቅም እንዳለው አስረድተዋል፡፡

በተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የከተማ ግብርና ትምህርት ክፍል የእንስሳት እርባታ አሰልጣኝ የሆኑት ወይዘሮ ባንቺአየሁ ጌታሁን እንዳብራሩት፤ የከተማ ግብርና ስራ ደጋፊ አንድ አካል የሆነው የመኖ አቅርቦት ነው፡፡ አንድ በከተማ ግብርና ዘርፍ ተሰማርቶ የሚሰራ አካል እንስሳትን ለማደለብ፣ የወተት ምርት ለማግኘት እንዲሁም ደግሞ የእንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በስፋት ምርት እንዲሰጡ ለማስቻል በዋናነት ከእንስሳት ምርት ጋር በተያያዘ የመኖ አቅርቦት ትልቁን ስፍራ ይይዛል ብለዋል፡፡

እንደ ተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የወተት ላም እና የእንቁላል ጣይ ዶሮዎች እርባታ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። ምርት በሚፈለገው ልክ ለማግኘት ከዚህ ቀደም መኖ ከውጭ በመግዛት ይጠቀሙ ነበር፡፡ ከዋጋ እንዲሁም ከጥራት አንፃር የመኖ ምርት ላይ የተወሰነ ክፍተት የታየ መሆኑን ተከትሎ ወደ መፍትሔው ለማቅናት በተደረገው ጥረት የመኖ ማቀነባበሪያ ማምረቻ ማሽን በውስጥ አቅም መስራት ላይ ደርሰዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ባንቺአየሁ ገለጻ፤ ለእንቁላል ጣይ ዶሮዎች የሚዘጋጀው መኖ ከውሃ ውጪ፤ በቆሎ፣ ፋጉሎ፣ ጨው፣ ፍሩሽካ እና ሌሎችን ጥረ ነገሮችን የያዘ መሆን አለበት፡፡ የሚቀነባበረውም ምግብ ሳይንሳዊ ሂደቱን መከተል ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለእንስሳቱ የሚሆነውን መኖ ለመሸመት 100 ኪሎውን በአራት ሺህ ብር ይገዙ ነበር፡፡ አሁንግን በውስጥ አቅም የመኖ ማቀነባበሪያ ማምረቻ ከተሰራ በኋላ አስፈላጊ የሆኑ የመኖ ግብዓቶችን በመግዛት በባለሙያ የተመጣጠነ ምርት በማምረት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳን ለእንቁላል ጣይ ዶሮዎች የሚሆነውን ምርት በኮሌጁ ማምረት ከተጀመረ አንድ ወር የተቆጠረ ቢሆንም በዶሮዎች ባህሪ ላይ ጥሩ ለውጥ ስለመታየቱ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ዶሮዎቹ እርስ በእርስ ይነካከሱ ነበር፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚሆነው ደግሞ የፕሮቲን እጥረት መከሰቱን ተከትሎ ይሁን እንጂ አሁን ላይ ዶሮዎቹ በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡ በእንቁላል ምርታቸውም ላይ በመቶ እጥፍ ጭማሪ አሳይተውናል የሚሉት ወ/ሮ ባንቺአየሁ፤ እንደ ተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ቁጥራቸው 750 ዶሮዎች ስለመኖራቸው አስታውቀዋል፡፡

በተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ዲን አቶ ወንድምሲያምረኝ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ አገልግሎት ተልዕኮውን ያደረገው በአካባቢው የሚገኙ ጥቃቅንና አነስተኛ፣ መካከለኛ እንዲሁም በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው የሚሰሩ ድርጅቶችን ሙያዊ ድጋፍ ከኮሌጅ ውጪ ሄዶ መስጠት ነው፡፡ ከሚሰጡ ድጋፎች መካከል የመዝገብ አያያዝ፣ የካይዘን ምርትና ምርታማነትን የማሻሻል የስነዘዴ ስልጠና ድጋፍ መስጠት፣ ኢንተርፕራይዞቹ ተሰማርተው በሚሰሩበት ስራ ሙያዊ ስልጠና እና ድጋፍ መስጠት እንዲሁም የኢንተርፕራይዞችን ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የሚረዱ፣ የውጪ ምርቶችን የሚተኩ እና የውጭ ምንዛሬን የሚያስቀሩ ቴክኖሎጂዎችን በኮሌጅ አሰልጣኞች አቅም ተሰርተው ወደ ኢንተርፕራይዞች እንዲሸጋገሩ ማስቻል ላይ እንደሚያተኩር አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ወንድሙ ገለፃ፤ ወቅቱ የእውቀት፣ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ስራዎች የሚበረታታበት መሆኑን ተከትሎ በርካታ ስራዎች ተከውነዋል፡፡ በአሰልጣኞች የተሰሩ ቴክኖሎጂዎች በተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ ተፈትሸው ውጤታማ መሆናቸው ሲረጋገጥ በአካባቢው የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ ማዕቀፍ የተያዙ ኢንተርፕራይዞች ላይ ሽግግር ይፈፀማል፡፡ እንደ ኮሌጁ ተጨባጭ ሁኔታ ከተሰሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች መካከል የእርጎ ማርጊያ ማሽን ተጠቃሽ ነው፡፡ የመስሪያ ማሽኑም በከተማ ግብርና ዘርፍ ተሰማርቶ ለሚሰራ ኢንተርፕራይዝም ተሸጋግሯል፡፡ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የቴክኖሎጂ ውጤቶች አይተኬ ሚናቸውን እየተጫወቱ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኮሌጁ በራሱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስራ ከመስራት አንጻር በከተማ ግብርና ስልጠና ዘርፍ ላይ እያገለገለ የሚገኘውን የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ አንዱ ስለመሆኑ የሚናገሩት አቶ ወንድሙ፤ የማቀነባበሪያ ማሽኑ ስራ ላይ መዋሉን ተከትሎ በወር ብቻ ከ500 ሺህ ብር በላይ ለማዳን ስለመቻሉ አንስተዋል፡፡ በተፈሪ መኮንን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የተሰሩ በርካታ የምርትና የማምረቻ ቴክኖሎጂ ስራዎች ወደ ኢንተርፕራይዞቹ ተሸጋግረው የውጪ ምንዛሬ ከማስቀረት ባሻገር ዜጎች ሀገራዊ ምርቶችን በማምረትና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ አበርክቷቸው የጎላ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review