ኢትዮጵያ እና ቻይና ያላቸውን የቆየ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር የመጀመሪያው የኢትዮ-ቻይና የቡና እና የንግድ ኮንፈረንስ በቻይና ተካሂዷል።
በዚሁ ጊዜ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ታዬ አጽቀሥላሴ እንዳሉት መድረኩ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ትስስር ከቡና ግብይት ባለፈ ወደ ሰፊ የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ነው።
የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑ እንደ ይርጋጨፌ፣ ሲዳማ፣ ካፋ እና ጅማ ያሉ የቡና ዝርያዎችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ የምትታወቅ መሆኗን ኘሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የቡናው ዘርፍ ለሀገሪቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ 25 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ ከውጭ ምንዛሬ ግኝት ደግሞ 30 በመቶውን በመሸፈን የኢኮኖሚው ዋነኛ የጀርባ አጥንት እንደሆነም ኘሬዚዳንቱ በመድረኩ አብራርተዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን በማንኛውም ሁኔታ የማይበገር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር ሹንዡዋ ከተማ ለኢትዮጵያ ቡና ወደ ሰፊው የቻይና ገበያ መግቢያ ዋና በር እንድትሆን ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በተጨማሪም የቻይናን የኢንዱስትሪ አቅም ከኢትዮጵያ የልማት ፍላጎት ጋር በማጣጣም ዘላቂ የንግድ ሥርዓት ለመገንባት ሀገራቱ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል።
ትብብሩ በግብርና ምርቶች እና በማዕድናት ላይ ብቻ ሳይወሰን፣ ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑባቸውን እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ፕሬዚደንት ታዬ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ ኮንፈረንስ ለኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ከመጨመር ባለፈ፣ ለወደፊቱ አፍሪካ የንግድ ትብብር እንደ አርአያ ሆኖ ያገለግላል ተብሎ ይጠበቃል።
በበረከት ጌታቸው