የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መንስዔ፣ መከላከያ እና ሕክምና

You are currently viewing የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መንስዔ፣ መከላከያ እና ሕክምና
  • Post category:ጤና

AMN – ታኀሣሥ 19/2018 ዓ-ም

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን በሽንት መውጫ ቱቦ ውስጥ ጀርሞችና ባክቴሪያዎች በመግባት የሚፈጠር የጤና እክል ሲሆን፣ በተገቢው ሁኔታ ካልታከመ እስከ ኩላሊት ድረስ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዩሮሎጂ (Urology) ሰብ-ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አሕመድ አበበ ስለ በሽታው መንስኤና መከላከያ መንገዶች በተመለከተ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ለሽንት ኢንፌክሽን ተጋላጭ የሚያደርጉ ሌሎች ምክንያቶች መኖር፣ የሰውነት ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ የሽንት መውጫ ጫፍ ከሰገራ መውጫ ጋር ቅርብ መሆኑ ባክቴሪያዎች በቀላሉ እንዲራቡ እና እንዲሰራጭ ያደርጋል።

በተለይም ሴቶች ከሽንት መውጫ እስከ ሽንት ፊኛ ያለው ርቀት አጭር መሆኑ ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው ዶክተር አሕመድ ገልፀዋል።

ህፃናት ሰውነታቸው ገና ስላልዳበረ እና በእድሜ የገፉ ሰዎች በሽታን የመከላከል አቅማቸው ደካማ መሆኑ ለበሽታው ተጋላጮች ያደርጋቸዋል።

በሽንት መስመር ላይ የጠጠር ወይንምስ የኩላሊት ጠጠር መኖር ባክቴሪያዎች እንዲራቡና ኢንፌክሽን እንዲከሰት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

በቀን ውስጥ ቢያንስ ከ 2 ሊትር በላይ ውሃ መጠጣት ባክቴሪያዎችን በሽንት ጠርጎ በማስውጣት በሽታውን ለመከላከል እንደሚረዳ ዶ/ር አሕመድ አስገንዝበዋል።

የሽንት መውጫ አካባቢን ከእርጥበትና ከሙቀት በመከላከል ንፅህናን መጠበቅ እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።

በተለይ ሴቶች ከተፀዳዱ በኋላ እርጥበት እንዳይኖር አካባቢውን በሚገባ ማድረቅ የሽንት ኢንፌክሽንን ለመከላከል ይረዳል።

ሽንት በሚመጣበት ጊዜ ወዲያውኑ መሽናት የሽንት ኢንፌክሽን እንዳይከሰት ይረዳል።

ሽንትን መቋጠር ባክቴሪያዎች በፊኛ ውስጥ እንዲከማቹ እና እንዲራቡ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ሽንት በመጣ ሰዓት መሽናት እንደሚገባም ባለሙያው አስረድተዋል።

አነቃቂ መጠጦችን በተለይ ካፌይን የበዛባቸውና አልኮል መጠጦችን መጠቀም የሽንት ፊኛን በማስቆጣት ለኢንፌክሽን ተጋላጭነትን ይጨምራሉ።

ያለ ሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰዱ ፀረ-ባክቴሪያ (Antibiotics) መድኃኒቶች የሰውነትን የመከላከል ባህሪ ስለሚያዛቡ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ዶ/ር አሕመድ አበበ አብራርተዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review