በአስገደ ወረዳና በህጻፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተረጂዎች ላለፉት አራት ወራት የሚገባቸውን ሰብአዊ ድጋፍ ሲያገኙ መቆየታቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች መኖራቸውን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማሪያም (ዶ/ር) ገለጹ።
ኮሚሽነሩ በአካባቢው የሚታየው የምግብ እጥረት ችግር የፌደራል መንግስትና አጋር አካላት ድጋፍ ስላላደረሱ ሳይሆን፣ የደረሰው ምግብ በአግባቡ ለተረጂዎች ፍጆታ ባለመዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ሽፈራው ተክለማሪያም (ዶ/ር) አክለው ቀደም ሲል በነበረው ልምድ፣ እርዳታው ተረጂዎች እጅ ከደረሰ በኋላ “በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ” በሚል ሰበብ ከድርሻቸው ላይ እህል የመቀነስ ተግባር በትህነግ ይፈጸም እንደነበርም ተናግረዋል።
ይህ ድርጊት ተረጂዎች የተሟላ ወርሃዊ ፍጆታ እንዳያገኙ በማድረግ ለችግር እያጋለጣቸው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በክልሉ በዓመት ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ ሰብአዊ ድጋፍ የሚቀርብ ቢሆንም፣ አሁንም በህጻፅና በሌሎች ጣቢያዎች ችግር አለ ተብሎ መቅረቡ የሄደው ሃብት የት ደረሰ? የሚል ጥያቄን ያስነሳል ነው ያሉት ዶክተር ሽፈራው ።
በዚህም ተረጂዎች መልሰው መቋቋም ሲገባቸው በየካምፑ እንዲቆዩ መደረጋቸውና ይህም ከምግብ እጥረት ጋር ተዳምሮ ጫናውን አክብዶታል የተባለ ሲሆን፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ከፕሪቶሪያው ስምምነት ያፈነገጡት የትህነግ ቡድን፣ የራሳቸውን የቤት ስራ ከመስራት ይልቅ፣ ችግሩን ለፖለቲካ ፍላጎት ማሳኪያነት እየተጠቀሙበት ነው የሚል ወቀሳም በተደጋጋሚ ይቀርብባቿልም ብለዋል።
በመሆኑም በየመጠለያ ጣቢያው የሚሰራጨው ምግብ አንድም ሳይቀር ለዜጎች መድረሱን ማረጋገጥ እንደሚገባም ሽፈራው ተክለማሪያም (ዶ/ር) አንስተዋል።
በወርቅነህ አቢዮ