ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ግንባታቸው የተጠናቀቁ 32 አዳዲስ የፖሊስ እና የእሳትና አደጋ ሥጋት መከላከያ ተቋማትን መርቀው ሥራ አስጀመሩ

You are currently viewing ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ግንባታቸው የተጠናቀቁ 32 አዳዲስ የፖሊስ እና የእሳትና አደጋ ሥጋት መከላከያ ተቋማትን መርቀው ሥራ አስጀመሩ

AMN ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ በአዲስ አበባ ፖሊስ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የተበሰረበት ዕለት ነው ብለዋል፡፡

በመዲናችን በሁሉም ክፍለ ከተሞች ግንባታቸው የተጠናቀቁ 32 አዳዲስ የፖሊስ እና የእሳትና አደጋ ሥጋት መከላከያ ተቋማትን መርቀን በይፋ ሥራ አስጀምረናል። በዚህም የፖሊስ መምሪያዎች፣ ጣቢያዎች፣ ካምፖች እንዲሁም የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከያ ተቋማት ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል፡፡

ይህ ተግባር በከተማዋ ፖሊሳዊና ድንገተኛ አደጋን የመከላከል አገልግሎቶችን ወደ ሕዝቡ ደጃፍ ይበልጥ ከማምጣቱም በላይ ነዋሪው በሰላም ግንባታና በአካባቢ ጥበቃ ሒደት ላይ በባለቤትነት ስሜትና በንቃት እንዲሳተፍ የሚያስችል ነው።

በተለይም እነዚህ ተቋማት በየአካባቢው መገንባታቸው ወንጀልን ለመከላከልና ድንገተኛ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት የሚሰጠውን የምላሽ ጊዜ በእጅጉ በማሳጠር፣ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመቀነስ ትልቅ አቅም ይፈጥራሉ በማለት ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱ መዲናችን ከደረሰችበት ፈጣን የዕድገት ደረጃ ጋር እንዲመጣጠኑ ተደርገው ከመገንባታቸውም በላይ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ አካታች መሠረተ ልማቶች ሲሆኑ እንዲሁም ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የታየባቸው፣ የሕፃናት ማቆያና ክሊኒክን ያካተቱ፣ እንዲሁም በዘመናዊ የመረጃ ማሰባሰቢያና የአደጋ መከላከያ መሣሪያዎች የተደራጁ ናቸው።

እነዚህ ፋይዳቸው ጉልህ የሆኑ ፕሮጀክቶች በታለመላቸው ጊዜና የጥራት ደረጃ እውን እንዲሆኑ ላስቻላችሁ ባለድርሻ አካላት በሙሉ፣ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review