የትራምፕ አስተዳደር በፈረንጆቹ 2025 ያደረገውን ከፍተኛ የውጭ ዕርዳታ ቅነሳን ተከትሎ፣ አሜሪካ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሁለት ቢሊየን ዶላር የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቷን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣን እንዳሉት፣ አሜሪካ ለተባበሩት መንግስታት ለሰብዓዊ ዕርዳታ ሁለት ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች።
አሜሪካ በዚህ ዓመት የዕርዳታ ወጪዋን የቀነሰች ሲሆን፣ እንደ ጀርመን ያሉ ግንባር ቀደም የምዕራባውያን ለጋሾችም የመከላከያ ወጪን በመጨመር ድጋፋቸውን ቀንሰዋል፤ ይህም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት አስከትሏል።
አሜሪካ ያደረገችው ድጋፍ እንዴት እንደሚመደብ ወይም ተጨማሪ ቃል ትገባ እንደሆን ዝርዝር ማብራሪያ አልተሰጠም።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በ2025 አሜሪካ ለተባበሩት መንግስታት የምታደርገው አጠቃላይ የሰብአዊ እርዳታ ወደ 3.38 ቢሊየን ዶላር ዝቅ ብሏል፡፡
ይህም 2024 ከነበረው 14.1 ቢሊየን ዶላር እና በፈረንጆቹ 2022 ከነበረው ከፍተኛው 17.2 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ በእጅጉ የቀነሰ መሆኑ ተነግሯል።
በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በፈረንጆቹ 2026 ለአደጋ የተጋለጡ 87 ሚሊየን ሰዎችን ለመድረስ 23 ቢሊየን ዶላር የዕርዳታ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ይህም በ2025 ከተጠየቀው 47 ቢሊየን ዶላር ግማሽ ያህሉ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የድጋፍ ፍላጎቶች ቢኖሩም የለጋሾች ድጋፍ ግን እየቀነሰ መምጣቱን ያሳያል።
የተባበሩት መንግስታት የዕርዳታ ዘርፍ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር እንደተናገሩት፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ምላሽ ከመጠን በላይ የተለጠጠ ቢሆንም በቂ የገንዘብ ድጋፍ ግን እንደሌለው መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህም ማለት አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ቅድሚያ ለመስጠት ቆራጥ ምርጫዎችን ማድረግ ያስፈልግ እንደነበር ገልጸዋል።
በታምራት ቢሻው