‎በ127 ሰዎች ላይ ከባድ የማታለል ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ

You are currently viewing ‎በ127 ሰዎች ላይ ከባድ የማታለል ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ

AMN -ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም

የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎችን እናስመጣለን በሚል በ127 ሰዎች ላይ ከባድ የማታለል ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ፡፡

ከከተማዋ መዘመን ጋር ተያይዞ ቀልጣፋና ተደራሽ የሆነ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት የተሳለጠ እንዲሆን መንግስትና ባለሀብቶች በዘርፉ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑ ይታወቃል።

በአንፃሩ ዜጎች ካላቸው ላይ ቆጥበው የነገ ህይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ በዚህ ዘርፍ ውስጥም ለመሰማራት ብዙ አማራጮችን ይፈልጋሉ፡፡

ይህንንም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዜጎችን በአነስተኛ ቅድመ ክፍያ የመኪና ባለቤት እናደርጋለን በማለት ከ127 ሰዎች ላይ ከ130 እስከ 350 ሺህ ብር የተቀበሉ ሁለት ተጠርጣሪዎችን በከባድ የማታለል ወንጀል ክስ ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል፡፡

አቶ ዳንኤል ዮሐንስ የሄሎ ታክሲ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ፣ ወይዘሪት እንግዳ የሺጥላ እና ሌሎች “መኪና አስመጪ ነን” ባዮችና ተባባሪዎቻቸው በፈፀሙት ከባድ የማታለል ወንጀል ክስ ክትትል ሲደረግባቸው እንደነበር ፖሊስ ገልጿል፡፡

ፖሊስ ግለሰቦቹ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ዜጎችን በማደራጀት በትንሽ ክፍያ የመኪና ባለቤት እናደርጋችኋላን በሚልና ባልተገባ መንገድ የበርካታ ዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ ጥለዋልም ብሏል፡፡

በአቋራጭ ለመክበር በማሰብ ከድሀው ዜጋ ገንዘብ በመሰብሰብ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚሹ ግለሰቦችም ይሁን ተቋማት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ያለው ፖሊስ መሰል የማታለል ድርጊት ውስጥ በሚገቡ ላይም ተገቢውን ህጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አሳስቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review