የላሽ በሽታ (Alopecia) እንዴት ይከሰታል? መፍትሔውስ?

You are currently viewing የላሽ በሽታ (Alopecia) እንዴት ይከሰታል? መፍትሔውስ?
  • Post category:ጤና

AMN ታኅሣሥ 21/2018

በድንገት የራስ ቅልዎ፣ ጺምዎ ወይም የአይን ሽፋሽፍትዎ ላይ ጸጉር በክብ በክብ እየሸሸ ወይም እየተመለጠ ተቸግረዋል? እንግዲያውስ ይህ የላሽ በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል።

ስለ ላሽ በሽታ ምንነት፣ ደረጃዎቹ፣ እንዴት እንደሚከሰት እና ህክምናውን በተመለከተ የቆዳና የአባላዘር ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶክተር ጽዮን ተስፋ፣ ከኤ.ኤም.ኤን (AMN) ጋር በነበራቸው ቆይታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የላሽ ህመም የራሳችን የነጭ የደም ሴል የጸጉር ዘለላን በሚያጠቃበት ጊዜ የሚፈጠር በሽታ ነው። ቦታው ላይ ያለውን ጸጉር የሚያሳጥር እና ጸጉር እንዳይበቅል የሚያደርግ ነው።

በሽታው ሁሉንም ሰው ያጠቃል፤ ጾታ እና እድሜ አይለይም። አንዳንዴ በእንቅርት እና ለምጽ ታማሚዎች ላይ በርከት ብሎ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

ላሽ እንዴት ይከሰታል?

ላሽ የሚከሰተው በዘር (በጄኔቲክስ) እና በአካባቢ ተጽእኖ ሊሆን እንደሚችል፣ እንዲሁም ምክንያቱ “ይሄ ነው” ተብሎ በውል እንደማይታወቅ ይገልጻሉ።

ምልክቶቹ፦

ከሌሎች የጸጉር በሽታዎች የሚለየው፡- ምንም አይነት ቁስል የለውም፣ የማሳከክ እና የመቅላት ስሜት አይኖረውም፣ ቦታው ላይ ጸጉር ስለማይኖር የጸጉር ዘለላ ነጠብጣቦች ብቻ ይታያሉ፡፡

የበሽታው ደረጃዎች፦

ላሽ ሶስት ደረጃዎች እንዳሉት የሚናገሩት ዶክተር ጽዮን፤ በራስ ቅል ላይ ብቻ በአንድ ቦታ ላይ ወይም ከአምስት ቦታ በታች ሲሆን እና መጠኑም ከአምስት ሴንቲ ሜትር በታች ከሆነ “አነስተኛው” ደረጃ ነው።

“መካከለኛ” የምንለው ደግሞ በራስ ቅላችን ላይ ከአምስት ቦታዎች በላይ ሲገኝ መሆኑን፣ እና

“ከፍተኛ” በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ በራስ ቅል ላይ ከአምስት ቦታዎች በላይ የሚገኝ ሆኖ፤ ሙሉ በሙሉ የራስ ቅልን፣ ጺምን እና የአይን ሽፋሽፍትን በሚያጠቃበት ጊዜ እንደሆነ ገልጸዋል።

መልካም ዜናው!

ይህ በሽታ ቦታው ላይ ጠባሳ ስለማይተው ጸጉር መልሶ የማደግ እድል አለው! በህክምና ሲታገዝ ደግሞ ለውጡ ፈጣን ነው።አዲስ የሚያድጉ ጸጉሮችም ከሌላው ለየት ብለው ነጣ የማለት እና ግራጫ ቀለም ይኖራቸዋል።

ህክምናው፦

እንደ ህመሙ ደረጃ በሀኪም የሚታዘዙ የሚቀቡ መድሃኒቶች ለመጀመርያው ደረጃ አይነት ህመም እንደሚሰጡ፣ ከዛ ከፍ ካለ ደግሞ ቦታው ላይ በመርፌ የሚሰጥ (በሀኪም የሚወጋ) መድሃኒት መኖሩን፤ እንዲሁም ደረጃው በጣም ከፍ ካለ የሚዋጥ መድሃኒትም እንደሚሰጥ ገልጸዋል። ህመሙ ሲያጋጥም የህክምና ክትትል በማድረግ መታከም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review