የሀገሪቱን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ ያለውን የእንጦጦ ፍተሻ – ሱሉልታ (20.3) ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ለማፋጠን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ቀደም ሲል መንገዱ የከተማ ክፍሎችን ሳይጨምር የነበረው 10 ሜትር ስፋት ለከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት የነበረ ሲሆን ፤ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንገዱ ወደ 50 ሜትር ስፋት እንዲያድግ ተደርጓል፡፡
ይህም በሁለቱም አቅጣጫዎች 28 ሜትር ከሚሸፍን የመኪና መተላለፊያ በተጨማሪ የሳይክልና የእግረኛ መሄጃዎችን ፣ የመንገዱን ጥራትና ዕድሜ የሚያራዝም ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት እንዲሁም የአካባቢውን ውበትና የአየር ንብረት የሚጠብቁ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ያካተተ መሆኑን አስተዳደሩ ገልጿል፡፡

በአሁናዊ የፕሮጀክቱ የሥራ ሂደት ላይም የአፈር ጠረጋ ፣ የቆረጣ ፣ የድልዳሎ እና የድጋፍ ግንብ ግንባታ ሥራዎች የትራፊክ ፍሰቱን በማያውክ ሁኔታ እየተከናወኑ ናቸው፡፡
የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ በመስመሩ ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በመቅረፍ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚደረገውን ጉዞ በእጅጉ ያቀላጥፋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሚገቡ የግብርና ምርቶችንና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ወደ መሃል ሀገር ለማጓጓዝ የሚያስችል መሆኑን ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡
ግንባታው በዓለምገና መንገድ ጥገና ዲስትሪክት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን ፤ የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የማማከርና ቁጥጥር ሥራውን እየሰራው ይገኛል፡፡