በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን የቤት አቅርቦት እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት፣ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸውና የተቀናጁ የተለያዩ የቤት ግንባታ አማራጮች በስፋት እየተተገበሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አማካሪ ኢንጂነር አውራሪስ ከበደ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ መንግስት የመዲናዋን ነዋሪዎች የቤት ፍላጎት ለማርካት ዘርፈ ብዙ ስልቶችን ቀርጾ ወደ ስራ ገብቷል ብለዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ እየተከናወኑ ካሉ የተቀናጀ የቤት ግንባታ አማራጮች መካከልም፣ በመንግስት በጀትና አስተባባሪነት የሚከናወኑ ግንባታዎች፣ በመንግስትና በግል ዘርፍ አጋርነት የሚገነቡ ቤቶች፣ በሪል ስቴት አልሚዎች የሚከናወኑ የቤት ልማቶች እና በማህበር በመደራጀት የሚገነቡ የቤት ልማት ፕሮግራሞች ተጠቃሽ መሆናቸን ኢንጂነር አውራሪስ ተናግረዋል፡፡
የግንባታ ሂደቱን ለማፋጠንና ጥራትን ለማረጋገጥ አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም አማካሪው ገልጸዋል።
በተለይም የስራ ባህላችንን በመቀየር ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በሳምንት ሰባት ቀናት፣ በቀን 24 ሰዓታት በከፍተኛ ትጋት እየተሰራ እንደሚገኝም ኢንጂነር አውራሪስ አስረድተዋል፡፡
አማካሪው አክለውም፣ ወጪን የሚቀንሱ፣ የግንባታ ጊዜን የሚያሳጥሩና ብክነትን የሚያስቀሩ ዘመናዊ የቤት ግንባታ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ገልጸው ይህም የከተማዋን የቤት ልማት ስኬታማ ለማድረግ ትልቅ አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።
ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚበቁ ቤቶች አሰጣጥን በተመለከተም፣ ቤት ለማግኘት ተመዝግበው ለረጅም ጊዜ ሲቆጥቡ የቆዩ ዜጎችንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ባካተተ መልኩ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ እንደሚከፋፈሉ አረጋግጠዋል።
የግል የቤት አልሚዎች በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በስራ ባህል መሻሻል ረገድ እያሳዩት ያለው ውጤታማ ተሳትፎ ለከተማዋ የቤት ልማት ትልቅ እሴት እየጨመረ መሆኑን ኢንጂነር አውራሪስ ከበደ ተናግረዋል፡፡
በአስማረ መኮንን