የዲሞክራቲክ ኮንጎ ደጋፊ የሆነው ’’በሕይወት ያለው ሃውልት’’

You are currently viewing የዲሞክራቲክ ኮንጎ ደጋፊ የሆነው ’’በሕይወት ያለው ሃውልት’’

AMN ታኅሣሥ 22 ቀን 2018 ዓ.ም

በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተከናወነ የሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውበቱን ጠብቆ እንደቀጠለ ነው፡፡ ውድድሩ በርካታ መነጋገሪያ ርእሶችን ቢሰጥም አንዳቸውም የዲሞክራቲክ ኮንጎ ደጋፊን ያህል አይሆኑም፡፡

’’በሕይወት ያለ ሃውልት’’ የሚል ቅፅል ስም ያገኘው ማይክል ኩካ ምቦላዲንጋ የውድድሩ ሌላ ቀለም ሆኗል፡፡ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ነፃነቷን እንድታገኝ ትልቅ አበርክቶ የነበራቸው የቀድሞ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓትሪስ ሉሙምባ ለማሰብ ያደረገው ድርጊት ዓለም አቀፍ እውቅናን አስገኝቶለታል፡፡

በመልክም ፓትሪስ ልሙምባን የሚመስለው ምቦላዲንጋ ሦስቱንም የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምድብ ጨዋታዎች ስታዲየም በመግባት ተመልክቷል፡፡

በሀገሪቱ የሚገኘው የፓትሪስ ሉሙምባ ሃውልት ቅርፅ በመምሰል ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳያደርግ ሦስቱንም ጨዋታዎች ጨርሶ ወጥቷል፡፡ ይህ ድርጊቱ ስታዲየም የታደሙ የሀገሩ ሰዎችን ጭምር አስደምሟል ፡፡ በርካቶችም ፎቶ ሲያነሱት ተስተውለዋል፡፡

ምድብ አራት ላይ የነበረችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሁለተኛ ደረጃ ይዛ በማጠናቀቅ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች፡፡ በጥሎ ማለፉም አልጄሪያን ትፋለማለች፡፡ ማይክል ኩካ ምቦላዲንጋም አስገራሚ ተግባሩን ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review