የ2018 የገና በዓል የተረጋጋ ግብይት እንዲኖረው አስፈላጊ ምርቶችን ለማቅረብ ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ እንዳስታወቁት የከተማ ነዋሪው በዓሉን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲያከብር ምርቶች ወደ ከተማው እንዲገቡ የማድረግ ዝግጅት አጠናቋል ብለዋል።
ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች እንዲሁም የእርድ እንስሳትን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ከሚመላከታው አካላት ጋር ዝግጅት ተጠናቋል ያሉት የቢሮ ሃላፊዋ በየደረጃው ምርቶቹ ለተጠቃሚዎቹ እንዲደርስም የቁጥጥር ስራዎች ይሠራሉ ብለዋል።
ለዚህም 279,620 የዳልጋ ከብቶችና 294,620 በግና ፍየል እንዲሁም 633,400 ዶሮዎችና 15,000,000 እንቁላሎች ከተለያዩ የከተማ መግቢያዎች እንደሚገቡ ሃላፊዋ ገልጸዋል።
በተጨማሪም 90,294 ኩንታል የሰብል ዓይነቶችና 416,205 ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶችም ለከተማው ነዋሪዎች እንዲቀርብ ይደረጋል ብለዋል።
በአለሙ ኢላላ