የ90ዎቹ የሕንድ ፊልሞች የትርጉም ንጉሥ

You are currently viewing የ90ዎቹ የሕንድ ፊልሞች የትርጉም ንጉሥ

AMN- ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያውያን የ1990ዎቹ ትዝታ ሲነሳ የህንድ ፊልም ትልቅ ስፍራ አለው።

ያ ዘመን የቪዲዮ ቤቶች የነገሱበት እና የቦሊውድ ተዋናዮች እንደ ሀገር ውስጥ ተዋናዮች የሚወደዱበት ልዩ ወቅት ነበር።

በየሰፈሩ “ቪዲዮ ቤት” ተብለው በሚጠሩ ትናንሽ ክፍሎች ውስጥ ተመልካች ለመሆን 50 ሳንቲም በመክፈል፣ አግዳሚ ወንበሮች ላይ ተፋፍጎ መቀመጥ የዘመኑ ዋነኛ መዝናኛ ነበር።

ፊልሙ ከመጀመሩ በፊት የሚመጡ የማስታወቂያ ምስሎች እና የፊልም አጫጭር ማስታወቂያዎች (Trailers) በራሳቸው ትልቅ ጉጉትን ይፈጥሩ ነበር።

በዚያን ዘመን በቪዲዮ ቤቶች ለበርካታ ተመልካቾች የህንድ ፊልምን ያስኮመኮመውና አይረሴ አሻራ ያኖረው ደግሞ ተርጓሚ ቃሲም መካ ነው።

የልጅነት ፍቅርና የትርጉም ሥራ ጅማሮ

ከኤ ኤም ኤን (AMN) መዝናኛ ጋር ቆይታ ያደረገው የልጅነታችን አስታዋሽ ቃሲም መካ፣ በዘርፉ ከ20 ዓመታት በላይ በመቆየት በበርካቶች ልብ ውስጥ ይኖራል።

ቃሲም ከ”ዋቢ ፊልም ፕሮዳክሽን” ጋር በመተባበር የህንድ ፊልምን ከእውቀት ጋር በመተርጎም የተመልካቾች የሳቅና የእምባ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።

የቦሊውድ የጥበብ ፈርጥ የሆነው የሻሩክ ካን (Shah Rukh Khan) ቀንደኛ አድናቂው ቃሲም፣ የትርጉም ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ለዓመታት ፊልሞችን ያለ ትርጉም ይመለከት ነበር።

ከሆሊውድ የአክሽን ፊልሞች ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ “ታርዛን” የተሰኘውን የህንድ ፊልም ያለ ትርጉም የተመለከተው የያኔው ትንሹ ቃሲም፣ በርካታ ፊልሞችን በመመልከት ቋንቋውን (ህንድኛን) መለማመድ ችሏል።

በመቀጠልም በራሱ ቪዲዮ ቤት “ኮይላ” (Koyla) የተሰኘውን የሻሩክ ካን ፊልም ለመጀመሪያ ጊዜ በመተርጎም ለተመልካች ማሳየት መጀመሩን ያስረዳል።

“የፍቅር ፊልም ማየት እንደ ሞኝነት ይቆጠር ነበር”

ለዝነኛው ተዋናይ ሻሩክ ካን ያለው ጥልቅ ፍቅር ቋንቋውን እንዲችል መነሳሳትን እንደፈጠረለት የሚናገረው ቃሲም፣ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ፦ “ያኔ ከካራቴ ፊልም ውጭ ልብ አንጠልጣይ የፍቅር ፊልሞችን የሚያይ ተመልካች እንደ ሞኝ ይቆጠር ነበር” ይላል።

በሥራው ወቅት ከተመልካች እኩል አብሮ ማንባትና መሳቅ ልምዱ መሆኑን የሚገልጸው ቃሲም፣ የሁለቱ አገራት (ኢትዮጵያና ህንድ) የባህል፣ የጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ የብዝሃነትና የማህበራዊ መስተጋብር መመሳሰል ኢትዮጵያውያን የህንድ ፊልም አፍቃሪ እንዲሆኑ ትልቅ በር መክፈቱን ያብራራል።

የህንድ ፊልም ለኢትዮጵያ የጥበብ ዘርፍ ያለው ፋይዳ

ለሻሩክ ካን ያለውን ጥልቅ አድናቆት የተረዱ ኢትዮጵያውያን፣ እንደ ዛሬው የፎቶ ማቀናበሪያ (Photoshop) ባልተስፋፋበት ዘመን የእርሱንና የተዋናዩን ፎቶ አቀናብረው የላኩለትን ጊዜ ሁሌም በደስታ ያስታውሰዋል።

ቃሲም እንደሚለው፣ ሻሩክ በብዙዎች ዘንድ ተፈቃሪ የሆነ የፊልሙ ዓለም ድንቅ ተዋናይ ነው።

የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውና የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል የሁለቱ አገራት ወዳጅነት በተግባር የታየበት መሆኑንም ቃሲም በቆይታው ገልጿል።

የቦሊውድ ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ፊልም ዕድገት

  • ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ፦ በአሁኑ ወቅት በሕንድ አንድ ፊልም ከሁለት ቢሊዮን የህንድ ሩፒ በላይ ፈሰስ ይደረግበታል።

ዘርፉ የአገርን ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባለፈ ራስን ለዓለም በማስተዋወቅ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል።

  • የራስ ቀለም፦ የቦሊውድ ፊልሞች በራስ ቀለም የተቀቡና ሙዚቃን ያቀላቀሉ በመሆናቸው ከሆሊውድ ቀጥሎ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ መፍጠር ችለዋል።

ይህንን ልምድ ወደ አገራችን በማምጣት ዘርፉን ማሳደግ እንደሚገባ መክሯል።

ውድ አንባብያን፣ የእናንተ የ90ዎቹ ትዝታስ የትኛው ፊልም ወይም የትኛው የቃሲም መካ ትርጉም ላይ ያርፋል? ሀሳብና አስተያየታችሁን አጋሩን።

በሚካኤል ኅሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review