በቡድን በመደራጀት የቤት ሰብሮ ስርቆት ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 10 ተጠርጣሪዎች ከተለያዩ ኤግዚቢቶች ጋር በቁጥጥር ስር ዋሉ

You are currently viewing በቡድን በመደራጀት የቤት ሰብሮ ስርቆት ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 10 ተጠርጣሪዎች ከተለያዩ ኤግዚቢቶች ጋር በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN ታህሳስ 23/2018 ዓ/ም

በቡድን በመደራጀት የቤት ሰብሮ ስርቆት ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 10 ተጠርጣሪዎችን ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ጊዜያት በመንቀሳቀስ የቤት ሰብሮ ስርቆት ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 9 ተጠርጣሪዎችን ከ1 ተቀባይ ግለሰብ ጋር በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው ሲሆን በአስሩም ተጠርጣሪዎች ላይ አቃቤ ህግ የምርመራ መዝገቦችን በመለየት ክስ እንደሠረተባቸው የለሚ ኩራ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ጣፎ ቅዱስ ገብርኤል መናፈሻ በተባለው አካባቢ የተፈፀመ የስርቆት ወንጀልን መነሻ በማድረግ ምርመራ መጀመሩን ያስታወሰው ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተከናወነው ተግባር አንዱን ተጠርጣሪ ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አውቶቡስ ተራ አካባቢ ለወንጀል መፈፀሚያ ከሚጠቀምበት የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2 – 73837 አ/አ ከሆነ ተሽከርካሪ ጋር ሊያዝም ችሏል።

ፖሊስ የመጀሪያውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር በማዋል ባደረገው ምርመራ የማስፋት ተግባር ሌሎች 8 ተጠርጣሪዎችን ወንጀል ለመፈፀም ይንቀሳቀሱበት ከነበረ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 B 01099 አ/አ ተሽከርካሪ ጋር በቁጥጥር ስር አዉሏል።

በተጨማሪም ግምታቸው ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ 11 ቴሌቪዥኖች፣ 6 የድራፍት በርሜሎች፣ የጸጉር ቤት ዕቃዎችና የተለያዩ ንብረቶችም ከአንድ ተቀባይ ጋር ተይዘዋል።

በተደጋጋሚ ጊዜ የሰዎችን እንቅስቃሴ በመከታተልና በተለይ በሌሊት ተንሸራታች (ሻተር) በሮችን በመክፈት፣ ተንጠልጣይ ቁልፎችን በመስበር የስርቆት ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደነበር ተጠርጣሪዎቹ በምርመራ ወቅት የእምነት ቃላቸውን ሠጥተዋል።

ፖሊስ የምርመራና የክትትል ቡድን በማዋቀር ሌት ተቀን ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ወንጀሉ ተፈፅሞባቸው ፖሊስ ጋር ሄደው ያላመለከቱ ግለሰቦች መኖራቸውንም ተጠርጣሪዎች መርተው ባሳዩት ሁኔታ መረዳት ተችሏል።

የቤታቸው አልያም የንግድ ቦታቸው በር ተሰብሮ ስርቆት ተፈፅሞብኛል የሚል ማንኛውም ግለሰብ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጎሮ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ በአካል ቀርበው ንብረታቸውን መምረጥ እንደሚችሉም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ መልዕክቱን አስተላልፏል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review