በአዲስ አበባ ከተማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ “የምርታማነት እምርታ ለዘላቂ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የገና በዓል ባዛር ተከፍቷል።
ባዛሩን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በይፋ ከፍተዋል።
በመርሐ-ግብሩም በሁሉም ክፍለ ከተሞች የገና በዓል ባዛሮች እየተከፈቱ እንደሆነና አቅርቦትን ከፍ በማድረግ እና ምርታማነትን በመጨመር የዋጋ ቅናሽ እንዲኖር ታሳቢ ተደርጎ የቀረበ መሆኑን አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል።

ባዛሮቹ ሁሉንም ምርቶች በአንድ ቦታ ላይ ለማግኘት የሚረዱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
አቅራቢዎች ምርቶችን በበቂ ሁኔታና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና በበኩላቸው በባዛሩ
130 ኢንተርፕራይዞች፣ 360 አንቀሳቃሾች እንዲሁም ህብረት ስራ ማህበራት እና ሌሎች አካላት እንዲሳተፉ መደረጉን ገልጸዋል።
በባዛሩ በቂ የምርት አቅርቦት መኖሩን የጠቆሙት ዋና ስራ አስፈጻሚው ምርቶቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የቀረቡ መሆኑንም ተናግረዋል።
በሀብታሙ ሙለታ