አርሰናል መሪነቱን ለማጠናከር ቦርንማውዝን ይገጥማል

You are currently viewing አርሰናል መሪነቱን ለማጠናከር ቦርንማውዝን ይገጥማል

AMN ታኅሣሥ 25 ቀን 2018 ዓ.ም

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ ሲጀመር አርሰናል ከሜዳው ውጪ ቦርንማውዝን ምሽት 2:30 ይገጥማል።

ማንችስተር ሲቲን በአራት ነጥብ በልጦ ሊጉን የሚመራው አርሰናል በቪታሊቲ ስታዲየም ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል። የሰሜን ለንደኑ ክለብ ከ22 ዓመት በኋላ በሊጉ ለመንገስ ጥሩ መንገድ ላይ ቢገኝም ጉዞው ገና ነው።

በሳምንቱ አጋማሽ አስቶንቪላን 4ለ1 የረታበት መንገድ አድናቆትን አትርፎለታል። በርካቶች ዋንጫው ወደ ኤምሬትስ የምሄድ እድሉ የሰፋ እንደሆነ በድፍረት መናገር ጀምረዋል። በዛሬው ጨዋታ በመድፈኞቹ በኩል ዴክለን ራይስ መግባቱ አልተረጋገጠም። ተከላካዮቹ ሪካርዶ ካላፊዮሪ እና ክሪስቲያን ሙስኬራ በጨዋታው እንደማይሳተፉ ሚካኤል አርቴታ ገልጿል።

የውድድር ዓመቱን በጥሩ ብቃት የጀመሩት ቦርንማውዞች በመጨረሻ ካደረጓቸው 10 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አንድም አላሸነፉም። ለአንዶኒ ኢራዮላ ቡድን ለዛሬው ጨዋታ ምናልባት ጥቂት ተስፋ የሚሰጠው ባለፈው የውድድር ዓመት በሁለቱም አጋጣሚ አርሰናልን ማሸነፉ ነው።

በቦርንማውዝ በኩል ኮከባቸው አንቷን ሴሜንዮ ለክለቡ የመጨረሻ ጨዋታውን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ጋናዊው ተጫዋች ማንችስተር ሲቲን ለመቀላቀል በግሉ ሙሉ ለሙሉ ተስማምቷል።

ዛሬ በሚደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች አስደናቂ ጉዞው በአርሰናል የተገታው አስቶንቪላ ኖቲንግሃም ፎረስትን ያስተናግዳል። በቪላ ፓርክ የሚከናወነው ጨዋታ ቀን 9:30 ይጀምራል።

ብራይተን ከ በርንሌይ እንዲሁም ዎልቭስ ከ ዌስትሃም ዩናይትድ በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ጨዋታቸውን ይጀምራሉ።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review