የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል

You are currently viewing የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል

AMN ታኅሣሥ 25/2018

በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ ዛሬ በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ይመለሳል።

በታንጀር ስታዲየም ሴኔጋል ከሱዳን ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። ሴኔጋል በምድብ አራት በሰባት ነጥብ የምድቡ መሪ በመሆን ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች።

በምድብ አምስት የነበረችው ሱዳን በሶስት ነጥብ በምርጥ ሶስተኝነት 16 ውስጥ ገብታለች። ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በሌሎች ውድድሮች ላይ ሰባት ጊዜ ተገናኝተው ሴኔጋል አራት ጊዜ ስታሸንፍ ሶስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ሴኔጋል በጨዋታዎቹ ስምንት ግቦች ስታስቆጥር ሱዳን አንድ ጎል ብቻ ከመረብ ላይ አሳርፋለች።

በሌላኛው የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ማሊ ከቱኒዚያ ምሽት አራት ሰዓት በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ይጫወታሉ። ማሊ በምድብ አንድ ያደረገቻቸውን ሶስት ጨዋታዎች አቻ በመለያየት በሶስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በምድብ ሶስት ተደልድላ ጨዋታዋን ያደረገችው ቱኒዚያ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች። ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ዋንጫ አራት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ማሊ ሁለት ጊዜ ስታሸንፍ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ቱኒዚያ እ.አ.አ በ1994 ባዘጋጀችው 19ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው ማሊ 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ሀገራቱ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ከሁለት ዓመት በፊት ኮትዲቯር ባዘጋጀችው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሆን በምድብ አምስት ተገናኝተው አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የዛሬ ጨዋታዎች አሸናፊ ሀገራት በሩብ ፍጻሜው ይገናኛሉ። የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር እስከ ታህሳስ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review