ኢትዮጵያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዩሮ ቦንድ ዕዳ ሽግሽግ ዙሪያ የመርሕ ስምምነት ላይ ደረሰች

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዩሮ ቦንድ ዕዳ ሽግሽግ ዙሪያ የመርሕ ስምምነት ላይ ደረሰች

AMN – ታኅሣሥ 24/ 2018 ዓ.ም

የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ ከታኅሣሥ 14 እስከ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ከባለድርሻ አካላት ኮሚቴ (Ad Hoc Committee) ጋር ባደረገው ዝግ ውይይት፣ የ1 ቢሊዮን ዶላር የ2024 የዩሮ ቦንድ ዕዳን በድጋሚ ለማዋቀር የሚያስችል በመርሕ ደረጃ የተመሠረተ ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቋል።

የስምምነቱ ውይይት ከ45 በመቶ በላይ የ2024 ቦንድ ይዞታ ያላቸውን ተቋማዊ ባለሀብቶች ከሚወክለው ኮሚቴ ጋር ሲሆን፣ በሂደቱም የኢትዮጵያ የሕግ እና የፋይናንስ አማካሪዎች (White & Case LLP እና Lazard) ተሳትፈዋል።

የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር ያላትን የፕሮግራም ግቦችና መለኪያዎች ያከበረ መሆኑ ተገልጿል። እንዲሁም የፓሪስ ክለብ እና የሌሎች ይፋዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ (OCC) የሚከተሉትን “የአበዳሪዎች እኩል አያያዝ” (Comparability of Treatment) መርህ የተከተለ ነው።

ኢትዮጵያ ስምምነቱን ለይፋዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ (OCC) እና ለዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ያሳወቀች ሲሆን፣ የዕዳ ሽግሽጉ የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ የዕዳ ዘላቂነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ለማረጋገጥ እየተሠራ ይገኛል ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው።

ሚኒስቴሩ በፋይናንስ ነክ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ ከኮሚቴው ጋር በቅንጅት የሚሠራ ሲሆን፣ የዕዳ ሽግሽጉን ተግባራዊነት በ2026 መጀመሪያ ላይ በሚከናወን የልውውጥ ጥያቄ (exchange offer) ለማፋጠን ቁርጠኝነት እንዳለው ገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስቴር በድርድሩ ወቅት ለነበረው ቀና ትብብር ለባለድርሻ አካላት ኮሚቴ እና ለአማካሪዎቻቸው ምስጋና ማቅረቡን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review