መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ የተከፈቱ ባዛሮች ሸማቾች ለበዓል ፍጆታ የሚፈልጉትን ምርት በአንድ ቦታ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ማስቻላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ገልጸዋል።
በየካ ክፍለ ከተማ የገና ባዛር ዛሬ በይፋ ተከፍቷል።
ባዛሩን የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የገና ባዛሮች መከፈታቸውን ገልጸው፣ ባዛሮቹ ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች በበቂ ሁኔታና የዋጋ ቅናሽ እንዲኖር ተደርጎ መቀረባቸውን ገልጸዋል።
ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች እንዲቀርቡ መደረጉን ወ/ሮ ሀቢባ ገልጸው፣ የዋጋ ጭማሪና ህገወጥነት እንዳይኖር የክትትልና ቁጥጥር ተግባር መጠናከሩን አክለዋል።
ባዛሮቹ ሁሉንም ምርቶች በአንድ ቦታ ለማግኘት የሚረዱ ሲሆኑ፣ ነዋሪዎች ከተመን በላይ ዋጋ የሚያቀርቡ ነጋዴዎችንና ህገወጥ ንግድን ሲመለከቱ ለሚመለከተው አካል መጠቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚና የስራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው አስራት በበኩላቸው፤ ክፍለ ከተማው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች መፈፀሙን ገልጸው፣ የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች በብዛትና በጥራት በተመጣጣኝ ዋጋ መቀረባቸውን ገልጸዋል።
ባዛሮቹ መዘጋጀታቸው ሸማቾች ለበዓል ፍጆታ የሚፈልጉትን ምርት በአንድ ቦታ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸውም ሸማቾች ተናግረዋል።
አቅራቢዎች ጥራት ያለው ምርት በበቂ መጠን እያቀረቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ባዛሩ ”በቂ የምርት አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም ሸማቾች ለገናችን” በሚል መሪ ሀሳብ የተከፈተ መሆኑም ተገልጿል።
በሔለን ጀምበሬ