በአዲስ አበባ ከተማ የገና በዓልን ታሳቢ በማድረግ የተከፈቱ ባዛሮች ለነዋሪዎች አማራጭ የገበያ መድረክ እየፈጠሩ መሆናቸው ተገለፀ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ እንዳሉት፣ እነዚህ ባዛሮች በአንድ በኩል ለነዋሪዎች አማራጭ ገበያ ሲፈጥሩ፣ በሌላ በኩል የደላላ ጣልቃ ገብነትን በመቀነስ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህዝቡ እያቀረቡ ነው።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የገና ባዛር በይፋ ተከፍቷል።

በዚሁ ጊዜ አቶ ሚሊዮን አዲስ አበባ ከተማ በልማትና በእድገቷ ልክ ሰው ተኮር የሆኑ ስራዎችን በትኩረት እየፈፀመች መሆኗን ገልጸዋል።
የተከፈቱ ባዛሮች መጭውን የገና በዓል ታሳቢ በማድረግ የገበያ አማራጭን ለማስፋት፣ የደላላ ጣልቃ ገብነትን ለመቀነስ እና ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ተመራጭ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሰው ተኮርና ገበያን የማረጋጋት ስራዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የከተማዋ መለያ እየሆኑ መጥተዋል ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ ምርታምነትን በማሳደግ፣ የገበያ አማራጭን በማስፋት እና ህገወጥነትን በመከላከል የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር በቀጣይም በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የገና ባዛሮቹ እስከ በዓሉ መዳረሻ ድረስ የሚቆዩ ሲሆን፣ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህዝቡ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በተመስገን ይመር