የምሁራንን አርበኝነት የሚሻውሀገራዊ ጉዳይ

You are currently viewing የምሁራንን አርበኝነት የሚሻውሀገራዊ ጉዳይ

“ምሁራን መፍትሔ አሳሽ መሆን አለባቸው”

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ድ/ር)

ኢትዮጵያ ያለፈ ታሪኳ ከባህር በር ጋር የተቆራኘ፣ የነገ ተስፋዋ ደግሞ ከአድማስ ባሻገር ካለው ሰማያዊው መንገድ ጋር የተሳሰረ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ። የታሪክ አጋጣሚዎችና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ገፍትረው ከባህር ዳርቻ አርቀዋት የሌሎች ሀገራት ጥገኛ አድርጓት እንጂ ኢትዮጵያ ለዘመናት የባህር በር ባለቤት ሆና መቆየቷን ታሪካዊ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡

ዛሬ ላይ ግን የባህር በር ጥያቄ ቅንጦት ፍለጋ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ሆኖ ከኢትዮጵያውያን ፊት ተደቅኗል። ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርባት ሀገር የባህር በር አልባ መሆኗ፣ የነገው ትውልድ የሚሸከመውን የታሪክ ዕዳ ከባድ ያደርገዋል። ይህ ችግር ከመድረሱ በፊት አሁን እንቅስቃሴ ተጀምሯል፤ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ የሁሉም ዜጋ በተለይም ደግሞ የምሁራን ብዕርና አዕምሮ ያስፈልጋል።

ምሁራን የታሪክን ጠባሳ መርምረው፣ የሕግና የዲፕሎማሲውን አቀበት አስተካክለው፣ በሰላማዊና በፍትሐዊ መንገድ ሰማያዊውን በሯን የምታንኳኳበትን የዕውቀት ካርታ የመንደፍ ታሪካዊ አደራ ወድቆባቸዋል። ይህ ጽሑፍም ኢትዮጵያ ከባህር ጋር ያላትን የቆየ ቁርኝትና ይህንኑ ታሪካዊ ግንኙነት ዳግም ለማጣመር ምሁራን ሊጫወቱት የሚገባውን ወሳኝ ሚና ይፈትሻል። አስቀድመን ግን አንዳንድ ምሁራንና ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን በዋቢነት በመጥቀስ ምሁራን የአንድን ሀገር ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቁ ረገድ ሊወጡት ስለሚገባው ኃላፊነት መረጃዎችን እንጥቀስ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ “የምሁራን ሚና ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል ርዕስ የጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ለሀገር ዕድገት ከምሁራን ጠንካራ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ጉዳዩን ሲያብራሩም፣ “ሀሳብ የለውጥ ኃይል ነው። ምሁራን ደግሞ የለውጥ ወኪሎች ናቸው። ምሁራን በማኀበረሰብ ውስጥ የሚፈጥሩት ለውጥም ሀገርን ወደ ብልጽግና ይወስዳል።” ብለዋል፡፡

ምሁራን ችግር ፈቺና መፍትሔ አሳሽ መሆን ይጠበቅባቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ምሁራን በስሜታዊነት የሚነዱ ሳይሆኑ ሀሳብ አክባሪና አፍቃሪ፣ ጥልቅ አሰላሳይ፣ አንባቢ፣ ችግር ፈቺና መፍትሔ አሳሽ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምሁራን በሁለንተናዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሚና በሚመለከት ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ የመደመር መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ላይ አይተኬ ሚና እንዳላቸው በጽኑ ያምናል፣ ለተግባራዊነቱም እየሰራ ይገኛል በማለት ገልፀዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)።

አያይዘውም ተቋማቱም የመማር ማስተማር እንዲሁም የምርምር ስራዎችን ከቴክኖሎጂ ጋር በማናበብ ወደ ፈጠራና ተግባር መለወጥ ይጠበቅባቸዋል። ይህም የኢትዮጵያን ብልጽግና በተደመረ አቅም ለማፋጠን ሚናው ከፍተኛ ስለመሆኑ አውስተዋል።

ምሁራን በዕውቀታቸውና በምርምር አቅማቸው የህብረተሰቡ አንቂ ተደርገው ይወሰዳሉ። በተለይ በአዳጊ ሀገራት ምሁራን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ የሀገር ግንባታ ዋና ተዋናይ መሆን እንዳለባቸውም ‘Bridge Builders: The Role of Intellectuals in Developing Countries’ የተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ሰፍሯል፡፡ በአንድ ሀገር የፖሊሲ ቀረጻ እና ስትራቴጂክ ውሳኔዎች ውስጥ የምሁራን ተሳትፎ አለመኖር ደግሞ በተቃራኒው ሀገሪቱን ለስሜታዊ እና ለጊዜያዊ ውሳኔዎች ተጋላጭ ያደርጋታል። ምሁራን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ፣ ሳይንሳዊ መረጃን መሠረት ያደረጉ የፖሊሲ ምክረ-ሀሳቦችን የማቅረብ ኃላፊነት አለባቸው። እንደዚሁም የተወሳሰቡ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በመተንተን ሀገሪቱ ልትከተለው የሚገባውን ዲፕሎማሲያዊ መስመር በማመላከት ረገድም ያላቸው ድርሻ ቀላል እንዳልሆነ በጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል።

አሜሪካዊው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ስቴፈን ክራስነር “Defending the National Interest” በሚለው መጽሐፋቸው፣ ብሔራዊ ጥቅም የአጭር ጊዜ የፖለቲካ ፍላጎት ሳይሆን የረጅም ጊዜ የሀገር ህልውና መሆኑን ይገልጻሉ። ምሁራን በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነውም ሆነ በገለልተኛነት፣ ከቡድን ጥቅም ይልቅ ለሀገር ዘላቂ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡ ፖሊሲዎችን የመቅረጽ ሚና እንዳላቸውም አመላክተዋል።

ብሔራዊ ጥቅም የሚጠበቀው በወታደራዊ ኃይል ብቻ ሳይሆን በባህል፣ በእሴቶች እና በዲፕሎማሲም ጭምር እንደሆነ ሳይንቲስቱ አመላክተዋል። አክለውም፣ ምሁራን ደግሞ የአንድን ሀገር ገጽታ በመገንባት፣ የባህል ተጽዕኖን በማሳደግ እና ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን የሚያመጡ የፖሊሲ አማራጮችን በማመንጨት ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑም ያብራራሉ።

ምሁራን በታሪክ፣ በጂኦ-ፖለቲካ እና በኢኮኖሚክስ ያላቸውን ዕውቀት በመጠቀም ሊመጡ የሚችሉ የውስጥ እና የውጭ ስጋቶችን አስቀድሞ የመተንበይ እና ለአደጋዎች የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የማዘጋጀት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የምሁራን ኃላፊነት በዚህ ደረጃ ከፍ ያለ ከሆነ ዘንዳ ለኢትዮጵያውያን የህልውና ጉዳይ ሆኖ ከፊት ለፊታቸው የተደቀነው የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ምን ሊሰሩ ይገባል? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ስለመሆኑ እንረዳለን፡፡

የኢትዮጵያ ምሁራን የባህር በር ጥያቄ በሚያነሱበት ወቅት “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ፤ ሂዱና ተዋጉ” የሚላቸው ሳይሆን “በጉዳዩ ዙሪያ ተባብረን እንስራ” የሚል መሪ ባለበት በዚህ ወቅት ሊወጡት የሚገባው ኃላፊነት ከፍተኛ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ እዚህ ጋር ሊነሳ የሚገባው ወሳኙ ጥያቄ ታዲያ ኃላፊነታቸው ምን ይሁን? የሚለው ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደህንነት መምህርና ከፍተኛ ተመራማሪው ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) ለዚህ ጥያቄ ምላሽ አላቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ የባህር በር አልባ ሀገራት መካከል በሕዝብ ብዛት ቀዳሚዋ ናት። ይህ ተፈጥሯዊ ጸጋ መታጣት ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለብሔራዊ ደህንነት እና ለጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ትልቅ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል። መንግስት የባህር በር ለማግኘት እያደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ጥረት ውጤታማ እንዲሆን የሀገሪቱ ምሁራን ሚናቸው ብዙ ነው፡፡

የአንድ ሀገር ብሔራዊ ጥቅም እንዲከበር ልዩነቶች ላይ ከመጠመድ ይልቅ አንድ በሚያደርግ አጀንዳ ላይ መስራት ያስፈልጋል የሚሉት ደግሞ የህግ ባለሙያው አቶ ኪያ ፀጋዬ ናቸው። የባህር በር ጥያቄውን አጠናክሮ መቀጠል፣ የተለያዩ አማራጮችን ማቅረብ እንደሚያስፈልግ የሚገልፁት የህግ ባለሙያው አቶ ኪያ በተለይም ምሁራን በውስጥ ያሉ ትናንሽ ችግሮችን እና ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም እንደሚገባ ያሳስባሉ።

ብዙውን ጊዜ የባህር በር ጥያቄ ከፖለቲካዊ ትርክት ጋር ብቻ ተያይዞ ይታያል። ሆኖም ምሁራን ይህ ጉዳይ ከእያንዳንዱ ዜጋ የዕለት ተዕለት ኑሮ ጋር ያለውን ትስስር ማሳየት አለባቸው። የኢኮኖሚክስ ምሁራን አንድ ምርት ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ የሚከፈለው የወደብ ኪራይ እና የሎጂስቲክስ ወጪ በሸማቹ ላይ የሚያሳድረውን ጫና በቁጥር አስደግፈው ማቅረብ አለባቸው። ለምሳሌ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ የሚወጣው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በሀገር ውስጥ ቢቀር ምን ያህል ፋብሪካዎችን መገንባት ይችል እንደነበር ማሳየት ህዝባዊ ንቃትን እንደሚፈጥር ሀሳባቸውን ያካፈሉን ምሁራን ያስረዳሉ።

የታሪክ እና የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ኢትዮጵያ ከባህር ጋር የነበራትን ጥንታዊ ቁርኝት እና የወደብ ማጣት በሀገራዊ ኩራት ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ በማስተማር፣ ጉዳዩ የትውልድ ጥያቄ መሆኑን ማስረፅ ይኖርባቸዋል። በመገናኛ ብዙሃን እና በትምህርት ተቋማት አማካኝነት ህዝቡ ስለ ሀገሩ ጥቅም ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ አለባቸው። ይህም ህዝቡ በስሜት ሳይሆን በእውቀት ላይ ተመስርቶ ሀገራዊ ጉዳዮችን እንዲደግፍ ወይም እንዲሞግት ይረዳል ይላሉ ሙሉጌታ (ዶ/ር)።

በእርግጥም ምሁራን ችግር ተናጋሪ ብቻ ሳይሆኑ መፍትሔ አመላካች መሆን አለባቸው። ለዚህም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በምን አይነት የኢኮኖሚ ውህደት ወይም የጋራ ልማት ስምምነት የባህር በር ማግኘት እንደሚቻል የፖሊሲ አማራጮችን ማመንጨት አለባቸው።  የባህር በር ከመገኘቱ በፊትና በኋላ ሊኖር ስለሚገባው የባህር ኃይል ዝግጁነት፣ የባህር ላይ ደህንነት እና የንግድ መርከቦች አስተዳደር ምሁራን የቅድመ ዝግጅት ጥናቶችን ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸውም አስተያየት ሰጪዎቹ ያስረዳሉ።

በሌላም በኩል የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥረት እንዲሳካ ምሁራን ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነፃ በሆነ መልኩ ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ሲሆን፣ መንግስትን በበሰለ ሀሳብና ጥናት የማማከር፣ ህዝቡን በሳይንሳዊ መረጃ ማንቃት እና  ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በዲፕሎማሲያዊ ጽሑፎች ማሳመን የምሁራኑ ኃላፊነት ስለመሆኑ አብራርተዋል የሰላምና ደህንነት ከፍተኛ መምህርና ተመራማሪው ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር)። ይህ ሲሆን የባህር በር የማግኘት ጥረቱ ከፍላጎት አልፎ ወደ ተግባራዊ ስኬት ሊቀየር የሚችልበትና ምሁራንም ታሪክ የሰጣቸውን አደራ ተወጥተዋል ማለት ይቻላል፡፡

በዓለም ላይ ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለው ሽኩቻ ከፍተኛ ነው፡፡ የቀጣናው የፀጥታ ሁኔታ ድንገት ቢደፈርስ ችግር ውስጥ የሚገባው የወጪ ገቢ ንግድ ስርዓቱ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ ደህንነት ጭምር ነው፡፡ “አንዳንድ ሀገራት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው መጥተው እኛ አፍንጫችን ላይ ባለ ነገር የበይ ተመልካች መሆን አይገባንም” የሚሉት ሙሉጌታ (ዶ/ር)፣ የባህር በር ጉዳይ ሸቀጥ ከማስገባትና ማስወጥ የተሻገረ የደህንነት ጉዳይ ስለመሆኑ በማስረዳት ህዝቡን ማንቃት የምሁራኑ ኃላፊነት ነው ይላሉ፡፡

ሙሉጌታ (ዶ/ር) በማጠቃለያ ሀሳባቸው ምሁራን ፈርጀ ብዙ ሚና እንዳላቸውና በአንድ በኩል እንደ ዜጋ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንደሚመለከታቸው ገልፀው፣ በሌላም በኩል የሞራልና የህግ ግዴታ እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል። ምሁራን ሊያደርጓቸው ይገባል ያሏቸውንም ጉዳዮች ጨምረው ሲገልፁ፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ ቀርበው መሞገት፣ እውነታቸውን ማስረዳት፣ የመጻፍና ጥናት ማድረግ፣ ኮንፈረንሶችን ማዘጋጀት፣ ሳይንሳዊ ሙግት ማቅረብም ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

አያይዘውም የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ምሁራን ዓለም አቀፋዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርበው ወደብ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፈው ማስረዳት እንዳለባቸውና በግለሰባዊ ብቻ ሳይሆን በተቋም ደረጃም ተደራጅቶ መስራት እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡

ሰሞኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው የ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርበው እንደገለፁትም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የውስጥ ልዩነቶችን የሚሻገር የትውልድ ጥያቄ ነው ብለዋል። አያይዘውም ኢትዮጵያ ያቀረበችው የባህር በር ጥያቄ የመንግሥት ወይም የአንድ ፓርቲ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ትውልድ ተሻጋሪ ግብ ያለው የትውልድ ጥያቄ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review