መንገድ ያገናኛቸው ፈላጊ እና ተፈላጊ

You are currently viewing መንገድ ያገናኛቸው ፈላጊ እና ተፈላጊ

የመንገድ መሰረተ ልማት መሟላቱ ያሻቸውን ያህል ምርት እንዲሸምቱ እድል እንደሰጣቸው ተጠቃሚዎች ገልጸዋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት በከተማዋ የመግቢያ በሮች የግብርና ምርቶች ማከፋፈያ የገበያ ማዕከላትን ገንብቶ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡ የገበያ ማዕከላቱ በዋናነት በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ የሚታየውን የደላላ ጣልቃገብነት ለማስቀረት እና ወደ ከተማዋ የሚገባውን ምርት በመጠንና በጥራት ለማሳደግ ታልሞ የተገነቡ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ማዕከላት መካከል ኮልፌ ሁለገብ የገበያ ማዕከል አንዱ ነው፡፡  

አዲስ ልሳን ጋዜጣ ቅዳሜ ጥቅምት 15 ቀን 2018 ዓ.ም “የተደበቀው የማዕከሉ አገልግሎት” በሚል ርዕስ ከቤተል ወደ ማዕከሉ የሚወስደው የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመጠናቀቁ ምክንያት ትራንስፖርት ወደ ማዕከሉ እንደማይገባና ለግብይት  ሂደቱም ማነቆ ሆኖ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በዚህ የተነሳ ነጋዴዎች ሱቃቸውን ዘግተው እስከመውጣት መድረሳቸውን  በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል፡፡ 

የመንገድ መሰረተ ልማቱ ችግሩ ምን ያህል እንደተፈታ እና የግብይት ሁኔታው ምን እንደሚመስል በድጋሚ ቅኝት ያደረገው የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል መንገዱ ተጠናቅቆ ስራ መጀመሩንና የትራንስፖርት አገልግሎትም ወደ ማዕከሉ መግባት መቻሉን ተመልክቷል። የመሰረተ ልማቱ መከናወን ማዕከሉ እየሰጠ ያለው የግብይት አገልግሎት እንዲሳለጥ ከማድረግ አንጻር ያለውን አበርክቶ ሸማቾችንና ነጋዴዎችን አነጋግሯል፡፡

ወጣት ልኡል ታያቸውን ያገኘነው በማዕከሉ ሽንኩርት፣ ካሮት እንዲሁም ጎመን ሲሸምት  ነው፡፡ “በየጊዜው እየመጣሁ የምፈልገውን ነገር  ለቤተሰቦቼ  እየገዛሁ እወስዳለሁ፡፡ የሚቀርቡት የፍጆታ ምርቶች ጥራት ያላቸውና ትኩስ ናቸው፤ ዋጋውም ቢሆን ውጭ ላይ ከሚገዛው ቅናሽ አለው፤ ይህንን እድል በሚፈለገው ልክ ለመጠቀም አስቸግሮን የቆየው ከቤተል ወደ ማዕከሉ የሚወስደው መንገድ የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖር ነበር፡፡ ሁሉንም ነገር ገዝቼ መሄድ እፈልግና ትራንስፖርት አለመኖሩን ሳስብ እቸገር ነበር” ሲል የሚያስታውሰው ወጣት ልኡል፤ በአሁኑ ወቅት መንገዱ ተስተካክሎ አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ፣ እሱም አቅሙ የሚፈቅደውን ያህል መግዛቱንና በዚህም ደስተኛ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ሌላኛዋ በማዕከሉ ግብይት ሲያደርጉ ያገኘናቸው ወይዘሮ ትዕግስት ነጋሽ ናቸው፡፡ ማዕከሉ ስራ ከጀመረ ጀምሮ የሚፈልጉትን ነገር ሸምተው እንደሚሄዱም ነግረውናል፡፡ ከዚህ በፊት ከማዕከሉ ሸምተው ወደ ቤታቸው ለመመለስ የትራንስፖርት ችግር ይገጥማቸው እንደነበር የሚናገሩት ወይዘሮ ትዕግስት፣ “በአሁኑ ወቅት ችግሩ ተቀርፎልናል፡፡ መንገዱ ተሰርቶ ባጃጆች እየገቡ ነው፡፡ በማዕከሉ የሚሸጡ አትክልት፣ ፍራፍሬ እንዲሁም ዘይትን ጨምሮ ውጭ ላይ ከሚሸጠው ቅናሽ አለው፡፡ ዘይት ባለ አምስት ሊትር በ1ሺህ 600 ብር ገዝቻለሁ፡፡ ውጭ ላይ ግን 1800 ብር እና ከዚያ በላይ ነው፡፡ ይህንን በቅናሽ  የገዛሁትን ዘይትም ሆነ  ሽንኩርት ይዤ በባጃጅ ተሳፍሬ ለመሄድ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ ይህ ለነዋሪው ማህበረሰብ ትልቅ እድል ነው፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ እኔ አቅመ ደካማና ተሸክሞ መሄድ ለማይችል መንገዱ ተሰርቶ ትራንስፖርት መግባቱ ጠቅሞናል” ሲሉ ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡

“የኮልፌ ሁለገብ የገበያ ማዕከል የነበረበት የመንገድ ችግር ተቀርፏል፡፡ ከዚህ በፊት የገዛነውን እቃ ወደ ቤታችን ይዘን መመለስ ስለማንችል በአካባቢያችን ከሚገኙ ሱቆች በውድ እንገዛ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ተሳፍረን መጥተን የምንሸምትበት እድል ተመቻችቷል” ሲሉም ያክላሉ፡፡

በማዕከሉ አትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ላይ የተሰማሩት አቶ ጤናዬ ዘርጋ በበኩላቸው፣ “የመንገድ መሰረተ ልማቱ ባልተሟላበት ወቅት ትራንስፖርት ስላልነበረ ኪሳራ ይፈጠር ነበር፡፡ ያመጣነውን ምርት በወቅቱ ለመሸጥ እንቸገር ነበር፡፡ ብዙ ጊዜም እየተበላሸ ደፍቻለሁ” ሲሉ ትውስታቸውን ነግረውናል፡፡

“በአሁኑ ወቅት ብዙ ሸማቾች ወደ ማዕከሉ ይመጣሉ፡፡ እኔም አትክልቱም ይሁን ፍራፍሬው ‘ይበላሻል’ የሚል ስጋት የለብኝም፡፡ የገዥዎች ቁጥር ሲጨምርም ውጤታማ እንሆናለን፡፡ ዋጋችንም ቢሆን በተቀመጠልን የዋጋ ተመን ነው የምንሸጠው፡፡ ይህም  ውጭ ላይ ከሚሸጠው ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ አለው” ሲሉም አክለዋል፡፡

 “ከዚህ በፊት ከማዕከሉ ወደ ቤተል አስፓልት የሚያስወጣው የመንገድ መሰረተ ልማት ለትራንስፖርት ምቹ አልነበረም፡፡ በዚህም ገበያው ተቀዛቅዞ ቆይቷል፡፡ ሱቃችንንም እስከመዝጋት ደርሰን ነበር፡፡ ሸማቾች ትራንስፖርት ወዳለበት ቦታ ነበር የሚሄዱት፡፡ በዚህም ደንበኞችን አሳጥቶን ቆይቷል። በስራችንም ውጤታማ እንዳንሆን አድርጎን ነበር” የሚሉት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ሙሉጌታ ጨቡዴ፣ “በአሁኑ ወቅት መንገዱ ተስተካክሎ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ነው። ሱቃችንንም ከፍተን እየሸጥን ነው። ሸማቾችም ወደ ማዕከሉ እየመጡ እየሸመቱ ይገኛሉ፡፡ ይህ መሆኑ ሸማቹም እኛም ተጠቃሚዎች ሆነናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ 

ሌላኛዋ የዘይትና አተር ክክ ምርትን ለህብረተሰቡ በማቅረብ ስራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ማህደር አስታወሰም የአቶ ሙሉጌታን ሃሳብ ያጠናክራሉ።፡ “የመንገዱ መሰራት ማህበረሰቡ ወደ ማዕከሉ በመምጣት የፈለገውን እንዲሸምት አድርጎታል፡፡ ይህ ሲሆን እኛም ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ ሱቅ ላይ ከሚሸጠው አንፃር ከ200 ብር ያላነሰ ቅናሽ እየሸጥኩ እገኛለሁ” ሲሉ ገልፀው፤ ይህን እድል ማህበረሰቡ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ 

አቶ መሃመድ አሚን የኮልፌ ሁለገብ የገበያ ማዕከል ስራ አስኪያጅ ናቸው። የገበያ ማዕከሉ የኑሮ ውድነቱን ማቃለልን እና የዋጋ ንረቱን ማረጋጋትን ዓላማ አድርጎ ከፍተኛ ወጭ ወጥቶበት ማህበረሰቡን ለማገልገል የተገነባ ነው፡፡ የሰብል ምርቶችን ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬዎች ከጋርመንት በማምጣት የግብይት እንቅስቃሴው እየተከናወነ ይገኛል፡፡ 

ሆኖም ከዚህ በፊት በመንገድ መሰረት ልማት መጓደል ምክንያት የገበያ መቀዛቀዝ ችግር ነበር፡፡ ሸማቾች ሸምተው ትራንስፖርት ስለማይገባ እቃቸውን ለማጓጓዝ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት መንገዱ ተስተካክሎ በቅርቡ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ይህ መሆኑ ማዕከሉ በሚፈለገው ልክ አገልግሎት እንዲሰጥ ያደርገዋል፡፡ ሸማቹም፣ ነጋዴውም  ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ 

ማዕከሉ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ፤ ውጭ ላይ ካለው ገበያ በቀነሰ ዋጋ በመሸጥ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግና ገበያውን ማረጋጋት ነው፡፡ ቅናሹም ከ15 እስከ 20 በመቶ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ፤  ይህንንም ለማስቀጠል በየቀኑ የፍጆታ እቃዎቹ በተለጠፈላቸው ዋጋ መሸጣቸውን እንዲሁም ጥራታቸውን ለማረጋገጥ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡

ሸማቹ ማህበረሰብ ትኩስ ምርቶችን ውጭ ላይ ከሚሸጠው ዋጋ ቅናሽ በሆነ መንገድ  እንዲሸምትና ተጠቃሚ እንዲሆን ማዕከሉ አገልግሎቱን በሚፈለገው ልክ እንዲሰጥ ባነሮችን የመስቀል፣ የማዕከሉን አቅጣጫ የሚያሳይ  ታፔላ የመለጠፍ፣ ባዛሮችን የማዘጋጀት እንዲሁም በማዕከሉ የሚቀርቡ ምርቶችን የሚያሳይ ትልቅ ስክሪን ግቢ ውስጥ የማስገባት ስራ ተሰርቷል፡፡ 

ማህበረሰቡም ከሩቅ ቦታዎች ሳይቀር በመምጣት የፍጆታ ምርቶችን ሸምቶ በመሄዱ ረገድ ጥሩ ውጤት እየመጣ ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ የትራንስፖርት አማራጩ እየሰፋ ሲሄድ የተሻለ ግብይት ይኖራል ተብሎ እንደሚታሰብ የሚናገሩት ስራ አስኪያጁ፤  ማህበረሰቡም በማዕከሉ መጥቶ እንዲሸምት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

በፋንታነሽ ተፈራ                

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review