በባዛሮች የሚከናወነው ሸመታ ምን መልክ አለው?

You are currently viewing በባዛሮች የሚከናወነው ሸመታ ምን መልክ አለው?

በአዲስ አበባ ከተማ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር በትኩረት መሰራቱ ተጠቁሟል

ባዛሮች ለኢኮኖሚ ዕድገት ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፤ ሰፊ የንግድ ልውውጥ የሚካሄድባቸው የኢኮኖሚ ሞተሮች ተደርገውም ይታሰባሉ። የስራ ዕድል መፍጠር፣ ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የንግድ መድረክ ማመቻቸት፣ የሸቀጦና አገልግሎቶች ዝውውርን ማፋጠን፣ የቱሪዝም መስህብ በመሆን የውጭ ምንዛሬ ማመንጭት ከብዙ የባዛር ጥቅሞች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ከሁሉ በላይ ባዛሮች ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ፣ በበቂ መጠንና በጥራት የሚግኙባቸው ስፍራዎች መሆናቸው ተመራጭ የገበያ ስፍራ ያደርጋቸዋል፤ በተጨማሪም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በማፋጠን፣ ድህነትን በመቀነስ እና የንግድ ትስስርን በማጠናከር ረገድም የማይተካ ሚና አላቸው። ባዛሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብም ያንቀሳቅሳሉ፡፡

በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሑፎችን የሚያስነብበው ‘ኢኮንስቶር’ (econstor) ገፀ ድር የባዛሮች ኢኮኖሚያዊ ድርሻ (Economic Role of Bazaars) በሚል ርዕስ ባወጣው መረጃ እ.ኤ.አ ከ2024 እስከ 2025 ባለው ጊዜ፣ የባዛሮች አካል የሆነው የዓለም የችርቻሮ ንግድ ድርሻ (Retail Market) ከ30 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚደርስ አስፍሯል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ2 ቢሊዮን በላይ ሰዎች መደበኛ ባልሆነው የንግድ ዘርፍ ውስጥ እንደሚገበያዩ የሚያትተው የ‘ኢኮንስቶር’ መረጃ፣ ባዛሮች የዚህ ዘርፍ ማዕከል እንደሆኑና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት፣ ዘርፉ ከሀገራቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ውስጥ እስከ 30 በመቶ  የሚሆነውን ድርሻ እንደሚይዝ ያመላክታል፡፡ ይህ ማለት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች በየቀኑ በእነዚህ ገበያዎች ውስጥ ይሽከረከራሉ እንደማለት ነውም ይላል።

በቱርክዬዋ ከተማ በኢስታንቡል ውስጥ የሚገኘው ግራንድ ባዛር የዓለማችን ትልቁ የባዛር ገበያ ሲሆን፣ በዓመት ከ90 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎችን ያስተናግዳል። በቀን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያንቀሳቅሳል። የመካከለኛው ምስራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ሀገራትም ትልልቅ ባዛሮች እንዳሏቸውና በዚህም ሸማቾቻቸው፣ ነጋዴዎቻቸውና ሀገራቱም ተጠቃሚዎች ስለመሆናቸው መረጃው ያትታል፡፡

አሁን አሁን የባዛር ግብይት በኢትዮጵያም እየተለመደ መጥቷል፡፡ በተለይ በበዓላት ሰሞን የባዛር ሁነቶች በስፋት ይታያሉ፤ ግብይቱም በዚያው ልክ ይጧጧፋል፡፡ ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊ በዓላት በሚከበሩባቸው ወቅቶች የምርት እጥረትና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳያጋጥም ባዛሮች ይሰናዳሉ፡፡ በሸማቾች ላይ ሊደርስ የሚችልን የኑሮ ጫና ለመከላከል መንግስት፣ የሸማችና የአምራች ማህበራት እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ ተናብበው የሚሰሩባቸው የባዛርና ኤግዚብሺን መድረኮች በስፋት ይዘጋጃሉ፡፡

መጪውን የገና በዓል አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡባቸው የገና ኤግዚቢሽንና ባዛር ዝግጅቶች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደ ክፍለ ከተማ ከተዘጋጁ የገና ባዛርና ኤግዚቢሽን መድረኮች መካከል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የተዘጋጀው ባዛር አንዱ ነው፡፡ በስፍራው ተገኝተን ባደረግነው ቅኝት የሞቀ የንግድ ልውውጥ ሲደረግ አስተውለናል፡፡

አጣና ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተዘጋጀው በዚህ ባዛር ሽንኩርት፣ ዘይት፣ እንቁላል፣ ዶሮ እና ሌሎች የግብርና ምርቶች በስፋት ቀርበዋል። ጫማና አልባሳትን ጨምሮ ሌሎች የኢንዱስትሪ ውጤቶችም እንዲሁ በየፈርጁ ተዘጋጅተዋል፡፡

በባዛሩ ግብይት ሲፈፅሙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ወሰን ታደሰ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ በበዓላት ሰሞን በሚዘጋጁ ባዛሮች እየተገኙ ሸመታ የማድረግ ልምድና ፍላጎት እዳላቸው ጠቁመው፣ ይህም እንዲህ ባሉት የገበያ ስፍራዎች ምርቶች በበቂ መጠን፣ ጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኙ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አቶ ዳዊት በርሄ የተባሉ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው በባዛሩ አልባሳት፣ የስጦታ እቃዎች፣ የምግብና መጠጥ ምርቶች፣ የቤት ዕቃዎች በአጠቃላይ ከበዓል ጋር ተያይዞ የሚሸመቱ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚቀርቡ ጠቁመው፣ በንፅፅር ከሌሎች የገበያ ስፍራዎች ባነሰ ዋጋ የሚፈልጓቸውን ምርቶች መሸመታቸውን ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ ዳዊት ገለፃ፣ ባዛሮች ከአቅርቦት አኳያ በጣም ጥሩ የሚባሉ ናቸው፡፡ ለበዓልም ሆነ ለእለታዊ ፍጆታ የሚፈለጉ ምርቶችን የማግኘት ዕድል ይሰጣሉ፡፡ ለትራንስፖርት የሚወጣ ወጪን በማስቀረት ብሎም ጊዜንና ገንዘብን በመቆጠብ ረገድም አጋዥ ናቸው፡፡

የገና በዓልን አስመልክቶ በተዘጋጀው ባዛር ላይ የቀረቡ ምርቶች በአካባቢያቸው ካለው ዋጋ አንፃር ተመጣጣኝና በአቅማቸው መሸመት የቻሉበት እንደሆነ ጠቁመው፣ ከዘይት ጀምሮ ሌሎች ማጣፈጫዎችና የልጆች አልባሳትን በተሻለ ዋጋ መግዛታቸውን ገልፀዋል፡፡ 

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልዋህድ በድሩ የበዓል ሰሞንን አስመልክቶ የምርት እጥረት እንዲሁም የዋጋ ንረት እንዳይከሰት የባዛሮች መዘጋጀት ወሳኝ እንደሆነ ገልፀው፣ አንደ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማም በሁለት ቦታዎች የገና ባዛር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

ባዛሮቹ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ለበዓል የሚያስፈልጋቸውን የፍጆታ እቃዎች ያለምንም እንግልት በተመጣጣኝ ዋጋ በቅርበት እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ በህገ ወጥና ስግብግብ ነጋዴዎች እንዳይበዘበዙ በማድረግ ረገድ አይነተኛ ድርሻ እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አጣና ተራ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተዘጋጀው ባዛር አስራ አምስት የሸማች ማህበራት፣ አንድ ዩኒየን፣ በግል የተደራጁ ኢንተር ፕራይዞች እና ሌሎች የንግዱ ማህበረሰብ ተሳታፊ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሃቢባ ሲራጅ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በበቂ መጠን በባዛሮች፣ በመንግስት የገበያ ማዕከላት እንዲሁም በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ለከተማዋ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡

የምርት አቅርቦት ዝግጅቱ ሁሉንም የፍጆታ ምርቶች ያካተተ ሲሆን፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ተፈላጊነታቸው የሚጨምሩ እንደ እንቁላል፣ ዶሮ፣ የዳልጋ ከብት፣ በግና ፍየል የመሳሰሉት ላይ ልዩ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ምርቶቹ ከመደበኛ ገበያዎች በተጨማሪ በንግድ ቢሮ፣ ህብረት ስራ ኮሚሽን፣ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን፣ ኢንዱስትሪ ቢሮ እና አዲስ አበባ ንግድ ስራች ድርጅት አስተባባሪነት በሚካሄዱ ባዛሮችና የግብይት መዳረሻዎች እንደሚቀርቡ ቢሮ ኃላፊዋ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ማብራሪያ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ 279 ሺህ 620 የዳልጋ ከብቶች እንዲሁም 294 ሺህ 620 በግና ፍየል በካራ አሎ፣ በአቃቂ፣ በብርጭቆ፣ በቄራና በሸጎሌ የቁም እንሰሳት የገበያ ማዕከላት ለግብይት ቀርበዋል፡፡

በተጨማሪም 633 ሺህ 400 ዶሮ፣ 15 ሚሊዮን እንቁላል፣ 90 ሺህ 294 ኩንታል የሰብል ምርቶች እንዲሁም 416 ሺህ 205 ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በግብይት ማዕከላቱ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለበዓሉ የቀረቡ ምርቶችን በአቅራቢያው በተዘጋጁ ባዛሮች፣ በመንግስት፣ የገበያ ማዕከላት እንዲሁም በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ግብይት እንዲፈፅም ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም ህብረተሰቡ በበዓል ግብይ ወቅት ህገ ወጥ ግብይትና የዋጋ ጭማሪ ካጋጠመው በቢሮው ነፃ የስልክ መስመር 8885 ላይ በመደወል ጥቆማ በመስጠት ህገ ወጥነትን እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።

በበዓላት ወቅት የሚዘጋጁ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች ለሸማቹ ማህበረሰብ ብቻም ሳይሆን ለነጋዴውም የተሻለ ገቢ ለማግኘትና አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት መንገድ የሚከፍቱ እንደሆኑ ተጠቁሟል።

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review