በ6 ሰዓት ቻርጅ ለ1 ወር 50 አምፖሎችን የሚያበራ ድምጽ አልባ ጄኔሬተር ስለ ሠራው ኢትዮጵያዊ ወጣት ከሰሞኑ የተሰራጨው መረጃ ብዙዎችን ማስደነቁ አልቀረም፡፡ ይህ ወጣት ፌደሳ ሹማ ይባላል፡፡ ለአዳዲስ ሃሳብ እና ቴክኖሎጂ ፈጠራ የታደለው ወጣቱ ከድምጽ አልባ ጄነሬተሩ በተጨማሪ 47 የሚደርሱ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ዕውን አድርጓል። በሥራዎቹም ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ በመቅረብ እውቅናና ሽልማትን አግኝቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በ2007 ዓ.ም በቻይና ቲያንዢን ከተማ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ የኤሌክትሪክ ችግርን የሚፈታ የፈጠራ ሥራ አቅርቦ ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም ደግሞ 9ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀበት ተሳትፎው ይጠቀሳል፡፡
እንደ ወጣት ፌደሳ ሹማ ዓይነት፣ እጅን በአፍ የሚያስጭኑ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን ዕውን ማድረግ የቻሉ በርካታ ትንታግ ኢትዮጵያውያን በብዛት አሉ፡፡ ሥራቸው የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ካገኘላቸው ጥቂት ባለ ተሰጥኦዎች ጀምሮ፣ በየትምህርት እና የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማቱ፣ የምርምር ማዕከላቱ፣ በግል ቤተ-ሙከራዎች (ወርክሾፖች)፣ በየጓዳ ጎድጓዳው አጃይብ የሚያሰኙ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች የሠሩትን ቤቱ ይቁጠራቸው። ለአካባቢ፣ ለከተማ፣ ለአገር አለፍ ሲልም ለዓለም ውስብስብ ችግር መፍትሄ ሊሰጡ የሚችሉ የታወቁም ሆነ የተደበቁ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ገሃድ ወጥተው ለውጤት የሚበቁበትን ዕድል ማመቻቸት የዘርፉ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡
ከላይ ያነሳነው ሃሳብ መንደርደሪያ በማድረግ፤ የአዳዲስ ቴክኖሎጂ መፍጠሪያ ማዕከላት ከሆኑት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት መካከል በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተሠርቶ ለአገልግሎት የበቃውን አንድ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤት ለማስቃኘት ወደድን፡፡ ቴክኖሎጂው ሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን የሚባል ሲሆን፤ የተለያየ የውፍረት መጠን ያላቸውን ብረቶች በተፈለገው ዓይነት ዲዛይን (ንድፍ) መቁረጥ፣ መብሳት፣ ቅርፅ ማውጣት የሚችል ነው። በኮሌጁ ለተቋቋመው ኢንተርፕራይዝ ውስጣዊ ችግርን ለመፍታት ታስቦ፣ የኮሌጁን አሠልጣኞች ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅሞ፣ በአነስተኛ ወጪ ተሠርቶ ለአገልግሎት የበቃው ይህ ማሽን፤ ብዙ የፈጠራ ውጤቶች የሚያጋጥማቸውን “የጋን ውስጥ መብራት” ሆኖ በመጋዘን (ስቶር) መቀመጥን ተሻግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የማኑፋክቸሪንግ ክፍል አሰልጣኝ መልኩ አበበ፣ ሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን ፈጠራ ላይ ከተሳተፉ እና ጉልህ ሚና ከተወጡ ተስፈኛ ሙያተኞች አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ አሰልጣኝ ከዚህ ቀደም በኮሌጁ ተሠርተው በተዋወቁ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች (ለአብነት፡- የዘይት ማቀነባበሪያ፣ የወርቅ ማጣሪያ፣ የ3ዲ የህትመት ማሽኖች …) ላይ ሙያዊ አሻራውን አሳርፏል፡፡ አሰልጣኝ እና የፈጠራ ባለሙያው ከጋዜጣችን ጋር በነበረው ቆይታ ስለ አዲሱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ጥልቅ ሃሳብና አስተያየት አጋርቶናል፡፡
አሰልጣኝ እና የፈጠራ ባለሙያው መልኩ አበበ እንዳስረዳው፤ ሲኤንሲ (CNC – Computer Numerical control) ስሙ እንደሚያመለክተው፦ ማሽኑ ተግባሩን የሚከውነው በኮምፒዩተር በሚሰጠው ኮድ አማካኝነት ነው፡፡ መጀመሪያ ማሽኑ እንዲሠራ የሚፈልገውን ሥራ ዲዛይን በመንደፍ ወደ ኮምፒዩተር የኮድ ቋንቋ ይለወጣል። ኮዶቹን የተቋሙ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ወደሆነው ሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን ይገባል፡፡ በኮምፒውተር ትዕዛዝ ማሽኑ ከስስ ላሜራ ጀምሮ እስከ 20 ሚሊ ሜትር የሚደርስ ውፍረት ያላቸውን ብረቶች በሚፈለገው ዓይነት ዲዛይን ይቆርጣል፣ ይበሳል፣ ቅርፅ ያወጣል፡፡
በ2017 የትምህርት ዘመን የተሠራው ቴክኖሎጂው፤ የፈጠራ ሃሳብ የመጣው ለችግር መፍትሄ ለመስጠት በሚደረግ ጥረት ውስጥ እንደሆነ አሰልጣኝ እና የፈጠራ ባለሙያው መልኩ አስታውሷል። ይህንንም ያብራራው፤ “ከዚህ በፊት በኮሌጁ የተሠሩትን በርካታ የፈጠራ ውጤቶች ለመሥራት በግብዓትነት የሚያገለግሉ ብረቶችን እና ላሜራዎችን በተዘጋጀው ዲዛይን መሰረት ለመቁረጥ ወይም ለመብሳት በውስጥ አቅም የማይቻል ነበር፡፡ ለዚህ መፍትሄ ከተቋም ውጪ ሌሎች ተቋማትን፣ ድርጅቶችን ወይም ግለሰቦችን እገዛ መጠየቅ ግድ ይል ነበር፡፡ ይህ አልሳካ ሲል ደግሞ፤ የተዘጋጀውን የወረቀት ላይ ዲዛይን ብረቱ ላይ በመሳል፣ የብረት መቁረጫ (ግራይንደር) ተጠቅሞ የሚፈልጉትን ቅርፅ ለማውጣት ጥረት ይደረግ ነበር። እነዚህ ጥረቶች በራሳቸው ውጤት ያመጡ ቢሆንም፤ ጥራት፣ ፍጥነት፣ ምርማነት የመሳሰሉትን ወሳኝ የቴክኖሎጂ አላባዊያን ያሟሉ አልነበሩም” በማለት ነው፡፡
“ችግር ብልሃትን ይወልዳል” እንደሚባለው ሁሉ፤ በተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ብረትን በግብዓትነት ተጠቅመው በሚሠሩ ቴክኖሎጂዎች ውጤታማነት እንቅፋት የሆነውን ችግር መፍታት ወሳኝ መሆኑን የተገነዘቡት የተቋሙ አሰልጣኞች እና የአመራር ስብስብ፤ የብረት መቁረጫ፣ መብሻ እና ቅርፅ ማውጫ ማሽን በራስ አቅም በመሥራት ለአገልግሎት ማብቃት ተገቢነት ላይ ስምምነት ደረሱ፡፡ ከዚያም አስፈላጊው የጥናት ሰነድ ተዘጋጅቶ ቴክኖሎጂውን በራስ አቅም ወደ መሥራት ተገባ፡፡ በመጨረሻም አስደናቂው ማሽን ከተሟላ ተግባሩ ጋር ዕውን ሆነ፡፡
በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተሠርቶ ለአገልግሎት የበቃው የሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን፤ የአልጋ ቅርፅ ያለው ሲሆን፤ ስፋቱ 3 ሜትር በ1 ነጥብ 5 ሜትር ነው፡፡ የሚጠቀመው የኤሌክትሪክ ኃይል ሲሆን፤ ብረትን ለመቁረጥ የሚያስችለውን በሙያ ቋንቋ አጠራር ፕላዝማ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። አጠቃላይ ማሽኑን ለመሥራት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የመሸጫ ዋጋ ተተምኖለታል፡፡ ይህንን ማሽን ከውጭ እናስገባ ቢባል ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ይፈጃል፡፡
ቴክኖሎጂው በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ውስጥ ወሳኝ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የጠቆሙት አሰልጣኝ እና የፈጠራ ባለሙያው መልኩ፤ “ከዚህ ቀደም ብረት ነክ የሆኑ ግብዓቶችን ወደ ተለያየ ዓይነት ቅርፅ ለመለወጥ ይታለፍ የነበረውን የመቁረጥ፣ የመብሳት እና ቅርፅ የማውጣት አድካሚ ሥራ አስቀርቷል፡፡ በአንፃሩ በፍጥነት፣ በጥራት፣ ወጪና ጉልበት በሚቆጥብ ሁኔታ ማከናወን ችሏል፡፡ በቀላል አነጋገር ይህ ማሽን ብረትን እንደ ወረቀት እየበሳ፣ እየቆረጠ፣ እየቀረፀ በቀላሉ ወደ ፈለግነው ዓይነት ውጤት መለወጥ እያስቻለን ነው” ብሏል፡፡
አክሎ እንዳብራራው፤ ማሽኑ ለብረታ ብረት እና መሰል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ትልቅ አቅም መፍጠር የሚችል ነው፡፡ ብረትን እና ሌሎች ግብዓቶችን ተጠቅመው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን ዕውን ለማድረግ ፍላጎት ላላቸው ሙያተኞች ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡ ጌጣ ጌጦችን የሚሠሩ ሙያተኞችንም ችግር በእጅጉ የሚፈታ፣ የሥራ ጥራታቸውን ውጤታማነት ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡ አንዳንዶች የሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን ለተለያዩ ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ያለውን አስፈላጊነት ሲገልፁት፤ ‘ማሽንን የሚያመርት ማሽን’ ይሉታል፡፡ ለምሳሌ ለግብርና ሥራ የሚያገለግሉ፡- ማረሻ፣ መኮትኮቻ፣ ማጨጅያ፣ መውቂያ የመሳሰሉትን ማሽኖች ለመሥራት ቢፈለግ፤ ለማሽኖቹ የሚያስፈልገውን ብረት በተዘጋጀው ዲዛይን አማካኝነት በፍጥነት፣ በጥራት እና በብዛት በማምረት ማሽኖቹን ለመሥራት ያግዛል፡፡
የሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን ለብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ዕድገት ቁልፍ አቅም ስለመስጠቱ፤ በተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ኢንተርፕራይዝ ውስጥ እያበረከተ ያለውን የምርታማነት እሴት ለውጥ ማሳያ ነው፡፡ በፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የማኑፋክቸሪንግ ክፍል አሰልጣኝ እና የአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዘሪሁን አየለ፤ በኮሌጁ የውስጥ አቅም የተሠራው እና ወደ ኢንተርፕራይዙ የተሸጋገረው ሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን እያበረከተላቸው ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ስለመሆኑ መስክረዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ሕጋዊ አሠራርን ተከትሎ የተቋቋመው የተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ኢንተርፕራይዝ በዋናነት በእንጨት፣ በብረታ ብረት፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት እንዲሁም በሌሎች የስልጠና ዘርፎች ያሉትን አቅም በመጠቀም ምርቶችን እያመረተ ለገበያ የማቅረብ ዓላማን በመያዝ እየሠራ እንደሚገኝ ያነሱት ሥራ አስኪያጁ፤ በአሁኑ ወቅት በብረታ ብረት እና እንጨት ምርቶች ላይ በተሻለ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዚህ ሥራ ውጤታማነት ላይ በኮሌጁ የውስጥ አቅም ተሠርቶ፣ ለኢንተርፕራይዙ በመሸጋገር ለአገልግሎት የበቃው የሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጁ ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ ዘሪሁን ገለጻ፤ የሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን ለተለያዩ የብረት ሥራዎች አጋዥ የሆነ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ትላልቅ መጠን ያላቸውን ብረቶች ለመቁረጥ፣ ለመብሳት፣ ቅርፅ ለመስጠት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በግራይንደር በመቁረጥ እና በመበየድ ለመሥራት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ሥራው ከፍጥነት፣ ከጥራት፣ ከምርታማነት እና ከውበት አንፃር የሚጠበቀውን ያክል አልነበረም፡፡ አሁን ላይ ይህ ማሽን በኮሌጁ አቅም ተሠርቶ ለኢንተርፕራይዙ በመሸጋገሩ ቀደም ሲል ይታይ የነበረውን ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ተቀርፏል፡፡ በቴክኖሎጂው በርካታ ምርቶችን ማምረት ተችሏል፡፡ ለአብነት በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገጠሙት ዘመናዊና ጠንካራ ከብረት የተሠሩ የቆሻሻ ማስወገጃዎች በብዛት፣ ጥራትና ውበት ባለው መልኩ የተሠሩትን ቴክኖሎጂውን በመጠቀም መሆኑን ማንሳት ይቻላል፡፡
የሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን (ቴክኖሎጂ) እንዲሸጋገርላቸው ለአዲስ አበባ ተግባረዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጥያቄ ካቀረቡ ኢንተርፕራይዞች መካከል የአቢሲኒያ ፍሌክሲብል ሜታል ኢንጂነሪንግ አንዱ ነው፡፡
የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተሾመ ተረፈ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፤ ተቋሙ ከውጭ የሚገቡ የቴክኖሎጂ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በሥራው ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂ ፈጠራና ልማት ላይ ትኩረት አድርገው ከሚንቀሳቀሱ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ተግባረዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አንዱ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኮሌጁ የተሠራውንና ለበርካታ ማሽኖች መሥሪያ አቅም የሚፈጥረውን የሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን (ቴክኖሎጂ) ሽግግር ለማድረግ የሁለትዮሽ ስምምነት ተደርሷል ብለዋል።
“ማሽኑ እንዲሸጋገርልን ፍላጎት የፈጠረብን ለምንሠራው ሥራ በጣም አስፈላጊ የሆነ፣ ከውጪ አገር ቢገባ ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ፣ በእኛ ቢመረት ለሌሎች መሰል ኢንዱስትሪዎች አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ነው” ያሉት አቶ ተሾመ፤ ከኮሌጁ ጋር የሰነድ ውል ስምምነት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
በከተማ አስተዳደር እና በፌደራል ደረጃ በተዘጋጁ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ሳምንት ላይ ለዕይታ በመቅረብ ሽልማቶችን እና ማበረታቻዎችን ያገኘው የሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን በመዲናዋ የሚገኙ በብረታ ብረት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች እንዲሠራላቸው ለአዲስ አበባ ተግባራ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ ካነጋገርናቸው አሰልጣኝና አመራሮች ማወቅ እና ከላይ የተጠቀሰውን ድርጅት በአስረጂነት መጥቀስ ይቻላል። እንዲህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂዎች ወደ አገልግሎት የመግባት ሁኔታ፤ ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በኮሌጁ የሚሠሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች በብዙ መመዘኛ ሲታዩ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመሻሻል ሂደት ላይ መሆናቸው ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ይህንን ውጤታማነት አጠናክረው በያዝነው የ2018 የትምህርት ዘመን በሚሠሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች ለማሳየት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡
በደረጀ ታደሰ