የመዲናዋ የጥበብ መሰናዶዎች

You are currently viewing የመዲናዋ የጥበብ መሰናዶዎች

በጊዜው አማረ

በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መርሃ ግብሮች መቅረባቸውን ይቀጥላሉ። ከእነዚህ መካከል የመጽሐፍ ምርቃት፣ የንባብ ውይይት፣ የሥዕል አውደ ርዕይ እና የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የተወሰኑትን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጽሐፍት

“አንድ አካል ሁለት አምሳል” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡  ደራሲው አዲስአለም አስቻለው ሲሆን፤ መጽሐፉ ልብ ወለድ ዘውግ ያለው የድርሰት ስራ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ አዲስአለም ከዚህ በፊት “ንግስት ዘውዲቱ” የተሰኘ ታሪካዊ ተውኔት መጽሐፍ ለአንባቢያን ማድረሱ ይታወቃል፡፡

በሌላ መረጃ በዛሬው እለት በደራሲ መስፍን ወንድወሰን “ሸሙኔ” መጽሐፍ ላይ ዳሰሳና ውይይት ይደረጋል፡፡ ይህ ውይይት በRotary Ethiopia Peace Center እና በብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት በትብብር የሚካሄደው ወርኃዊ መርሐ ግብር አካል ነው፡፡ ውይይቱ ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት እስከ 6:30 ሰዓት በብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት (ወመዘክር) ይካሄዳል፡፡ ይህ መርሐ ግብር ሥነ-ጽሑፍ ለሰላም ግንባታ ያለውን የማይተካ ሚና የሚያሳይ ልዩ ዝግጅት መሆኑንም አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም  “የጨረቃ ብርሃን” ግለ-ታሪክ መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ መጽሐፉን ያዘጋጁት አድሀኖም ምትኩ እና ዮሐንስ አዝመራው ሲሆኑ፤ የወይዘሮ ብርሃኔ አስፋውን ታሪክና አበርክቶ የያዘ ነው፡፡ ባለታሪኳ ወይዘሮ ብርሃኔ አስፋው ከ80 በላይ የዓለም ሀገራት በማቅናት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲወገዱ ለ60 ዓመታት ትግል አድርገዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ  በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የህፃናት መብት ስምምነት እንዲፀድቅ የበኩላቸውን ሚና የተጫወቱ ናቸው። በአፍሪካ ህብረት የማፑቶ ፕሮቶኮል ውስጥ ጎጂ ልማዶችን የሚከለክሉ አንቀፆች እንዲካተቱ ታላቅ ተጋድሎ እንዳደረጉ የተወዳጅ ሚዲያ ዘገባ ያሳያል፡፡

የውይይት መርሃ ግብር

“ሰው እና ጉዞ“ በሚል ርእስ  ልዩ የፓናል ውይይት በዛሬው እለት ይካሄዳል፡፡ በዚህ መርሃ ግብር ውይይት ሃሳብ የሚያቀርቡት ደራሲና ተርጓሚ ዶክተር ጌታቸው ተድላ፣ ተጓዡ ጋዜጠኛና ደራሲ ሄኖክ ስዩም፣ ደራሲ ፍቃዱ አየልኝ እንዲሁም ደራሲ እና ተመራማሪ ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ ሲሆኑ ውይይቱ  በደራሲ ይታገሱ ጌትነት መሪነት ይካሄዳል፡፡ መርሃግብሩ  4 ኪሎ ኢክላስ ሕንጻ፣ ከ8:00 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል፡፡

ሙዚቃ

የድምፃዊ ታሪኩ ጋንካሲ አዲስ ነጠላ ሙዚቃ ተለቀቀ፡፡ “ቦቦ” የተሰኘው ይህ ሙዚቃ በትናንትናው እለት ማታ በናሆም ሬከርድስ አማካኝነት ለአድማጭ ተመልካች ይፋ ሆኗል፡፡ ድምጻዊ ታሪኩ ከዚህ ቀደም ጦና ጋጋሶ፣ ያኔ  እና  ዲሽታ ጊና የተሰኙ የሙዚቃ ስራዎችን ለህዝብ አድርሷል፡፡

የቴአትር መርሃ ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ።  በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቅዳሜ ሁለት ቴአትሮች ማለትም 8፡30 ሰዓት ላይ 12ቱ እንግዶች እንዲሁም 11፡30 ሰዓት ባሎችና ሚስቶች ለእይታ ይበቃል። እሁድ በ8፡30 ሰዓት ንጉሥ አርማህ ቴአትር፣ እንዲሁም  እምዩ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በ11፡30 ሰዓት ላይ ይታያሉ፡፡ በሀገር ፍቅር ደግሞ  “የመጨረሻው ፍርድ” ቴአትር እሁድ 11:30 ሰዓት ይታያል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review