“የገና በዓልን ከመዝናኛ ስፍራዎች በአንዱ የማክበር እቅድ አለኝ”
ወጣት ኤልያስ ተስፋ
እሰይ መጣልን አውዳመት
እንደሰት
የክት ልብስሽን ልበሽ እናታለም
ዛሬኮ አውዳመት ነው ሌላ ስራ የለም… ትላለች ድምጻዊት አምሳል ምትኬ አውዳመት በተሰኘው ሙዚቃዋ፡፡
ይህ ሙዚቃ የሚያስተላልፈው አንድ መልዕክት አለ፤ ይህም የሰው ልጅ ሕይወት ከሥራ፣ ከትምህርት፣ ከቤተሰብ ኃላፊነትና ከማኅበራዊ ግዴታ ጋር የተቆራኘ መሆኑን። በዓላት ከእነዚህ የዕለት ከዕለት ኃላፊነቶች እና ስራዎች ጫና ለመላቀቅ፣ አዕምሮን ለማደስ እና አካልን ለማሳረፍ የሚያስችል ወሳኝ ዕድል ይፈጥራሉ። በተጨማሪም በዓላት ጤናማና ፍሬያማ ሕይወት ለመምራት፣ የእምነት ግዴታን ለመፈጸም የሚያስችሉ መሠረታዊ ነገሮች ናቸው።
ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት የአንድን ማህበረሰብ ማንነትና ትውስታ የሚጠብቁ፣ በየጊዜው የሚመጡ እንዲሁም የሚናፈቁ ናቸው። በአብዛኛው የዓለማችን ክፍል፣ በዓላት ከዕለት ተዕለት ኑሮ ወጣ ብሎ በጋራ የሚከበሩ ልዩ ጊዜን እና የተዝናኖት እድልን የሚጨምሩ ናቸው። እነዚህ ጊዜያት ልዩ የመዝናኛ አማራጭን በመፍጠር ረገድ ተወዳዳሪ አይገኝላቸውም።
በዓላት የሚፈጥሯቸው የመዝናኛ አማራጮች እንደየበዓሉ ዓይነት ይለያያሉ። ለምሳሌ፡- የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ በዝማሬ የሚከበር መንፈሳዊ በዓል ሲሆን፣ የገና በዓል ደግሞ በቤተሰብ መካከል የስጦታ ልውውጥ የሚታይበት፣ በቤት ውስጥ የሚከበር ነው። በዓሉ ሩቅና ቅርብ ያሉ ዘመድ አዝማዶችን፣ ጎረቤትና ወዳጆች የሚሰባሰቡበት ድልድይም ነው።
በዓል ሲመጣ ከሩቅ ከተሞችና ከውጭ ሀገር የሚመጡ የቤተሰብ አባላት መኖሪያ ቤቶችን በደስታ ይሞሉታል። አዛውንቶች የልጅ ልጆቻቸውን ሲያዩ፣ ትውልዶች የጋራ ትውስታን ሲፈጥሩ፣ የቤተሰብ ፍቅርና ትስስር ይጨምራል። ሳቅና ጨዋታ ይደራል፡፡ በበርካታ ሀገራትና ከተሞች ደግሞ የገና በዓልን በተለይ ከሰዓት ከቤት ወጣ ብሎ በመዝናኛ ቦታዎች ማክበር የተለመደ ነው፡፡
ለመሆኑ የአዲስ አበባ እህት ከተሞች የገና በዓልን እንዴት ያከብሩታል፡፡ በዓሉን ከቤት ወጣ በማለትና በመዝናኛ ስፍራዎች የማክበር ባህላቸው ምን ይመስላል። በአዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በበዓላት ዕለት በተለይ ከሰዓት በመዝናኛ እና በመናፈሻ ቦታዎች የማክበር ልምድ ምን ይመስላል የሚለውን በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
ከኮሪደር ልማቱ በፊት በአዲስ አበባ ውስጥ ለመዝናኛነት ሲታሰብ አብዛኛው አማራጮች የተወሰነ ክፍያ የሚጠይቁ ሆቴሎች፣ ካፌዎች ወይም ጥቂት የታጠሩ ፓርኮች ነበሩ። ይህ ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማህበረሰብ ከዘመናዊ መዝናኛዎች ያገለለ ነበር።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም በአዲስ አበባ የከተማ እድገት፣ ለውጥ እና መዝናኛ አማራጮች መስፋፋት ጋር ተያይዞ በዓላትን ከሰዓት በኋላ ከቤት ወጥቶ በመዝናኛና በመናፈሻ ስፍራዎች የማሳለፍ ልምድ እየተለመደ መጥቷል። የቀድሞው በቤት ብቻ የመታጠር ባህል እየተቀየረ አዲሶቹ የመዝናኛ አማራጮች (እንደ አንድነት እና እንጦጦ ፓርኮች፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ) በዓል አድማቂ መድረኮች እየሆኑ ነው። ቤተሰቦችና ወጣቶች ቀኑን ሙሉ በቤት ውስጥ ከዋሉ በኋላ ከሰዓት ገደማ በመናፈሻዎች በመገኘት አየሩን በመቀበል፣ ፎቶ በመነሳት፣ በመጫወቻ ስፍራዎች ጊዜ በማሳለፍ እና ከጓደኞቻቸው ጋር በመገናኘት በዓሉን ሲያከብሩ መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡
ይህ አዝማሚያ የከተማዋን ፈጣን ለውጥ ከማሳየቱም በላይ፣ የከተሜነት (urbanization) ተጽዕኖ በበዓል አከባበር ባህል ላይ የሚያመጣውን ለውጥ ያሳያል። ወጣቱ ትውልድም ሆነ፣ እናት እና አባት ህጻናት ልጆቻቸውን በመያዝ በበዓል ቀን ከሰዓት በኋላ በመዝናኛ ስፍራዎች የመዝናናት ልምድና ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱንም መረዳት ይቻላል።
ወይዘሮ መሰረት ተካልኝ የአዲስ አበባ ነዋሪ እና የሶስት ልጆች እናት ናቸው። ወይዘሮ መሰረት ለረጅም ዓመታት የገናን በዓል የሚያከብሩት በተለመደው የቤት ውስጥ ድባብ ነበር። ጠዋት ቤተ ክርስቲያን መሳለም፣ ቀጥሎም ቤት ገብቶ ማዕድ ማዘጋጀት፣ ከዘመድ አዝማድ ጋር መቋደስ… ይህ የማይለወጥ የሕይወታቸው አካል ነበር።
“ለእኔ በዓል ማለት ቤት ውስጥ ተሰባስቦ ሲጨዋወቱ፣ ሲበሉና ሲጠጡ መዋል ነበር” ይላሉ ወይዘሮ መሰረት ትናንትን ሲያስታውሱ። ነገር ግን ልጆቼ እያደጉ ሲመጡና ከተማዋም ስትቀየር፣ ከቤት ወጣ ብለን ማክበር ጀመርን። ለአብነትም ባለፈው ዓመት ከሰዓት የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከልጆቼ ጋር ሄጄ ነበር፡፡ በርካታ ሰው ነበር የነበረው። በፋውንቴኑ የሚዝናና እንዲሁም ፎቶ የሚነሳ በርካታ ሰው ነበር፡፡ እኛም ደስ የሚል ጊዜ ነው ያሳለፍነው ይላሉ፡፡
ወጣት ኤልያስ ተስፋ አዲስ አበባ መኖር ከጀመረ 10 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ እርሱም በዓላትን ከቤት ውጭ ከሚያከብሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ኤልያስ፣ “ከቤተሰብ ርቄ መኖር ከጀመርኩ ብዙ ዓመታት እየሆነኝ ነው። የመጀመሪያዎቹን ዓመታት በጣም ነበር የምቸገረው፡፡ ምክንያቱም ብዙ የምሄድበት ቦታ አልነበረም፡፡ አሁን ግን በዓልን በመዝናናት ለማሳለፍ በርካታ አማራጮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከሁለት ዓመት በፊት ከጓደኞቼ ጋር እንጦጦ ሄደን ነበር፡፡ አምናም የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሄጂ ነበር፡፡ ይህ የመዝናኛ ስፍራ በዓልን በቤት ውስጥ ከማሳለፍ በተጨማሪ ሌላኛው አማራጭ ሆኖኛል” በማለት ልምዱን ያጋራል፡፡
በእርግጥ በአብዛኛው የአደጉ ሀገራትም በዓልን ከቤት ወጣ ብሎ በፓርኮችና በሚጎበኙ ቦታዎች በመዝናናት ማክበር የተለመደ ነው፡፡ በአብዛኛዎቹ የአውሮፓና አሜሪካ ከተሞች (ለምሳሌ የአዲስ አበባ እህት ከተማ በሆነችው ዋሽንግተን ዲ.ሲ.) የገና በዓልን ከቤተሰብ ጋር፣ ስጦታ መለዋወጥ፣ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ ይከበራል፡፡ በተጨማሪም በዓሉን ምክንያት በማድረግ ትልልቅ የመብራት ጌጦች፣ የገና ገበያዎች እና የልዩ ዝግጅቶች የሚካሄዱ ሲሆን፣ ሰዎች በዓሉን ለማድመቅ ወደ ውጪ ወጥተው እነዚህን ዝግጅቶች የመጎብኘት እና በፓርኮች የመዝናናት ጠንካራ ባህል አላቸው።
ሌላኛዋ የአዲስ አበባ እህት ከተማ በሆነችው የሩዋንዳዋ ኪጋሊም የገና በዓልን በእርድ፣ ቤተሰብ በመጠየቅ ይከበራል፡፡ ከሰዓት ደግሞ ቤተሰቦች፣ ጓደኛሞችም ሆነ በግል በውብ የመዝናኛ ስፍራዎች እና ፓርኮች የገና በዓልን ማክበር የተለመደ ነው፡፡
በሀገራችን የገና በዓል ሲመጣ ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው የቄጤማው መዓዛ፣ የዶሮ ወጥ ሽታ እና የቤተሰብ ጨዋታ እና ጥየቃ ነው። አዲስ አበባ ያለው ገጽታም በሀገር ደረጃ ካለው የተለየ አይደለም፡፡ ነገር ግን በጊዜ ሂደት የአዲስ አበባ ገጽታ ሲቀየር፣ የበዓል አከባበር ልምድም አብሮ እየተቀየረ ይገኛል። ከእነዚህ ለውጦች መሃል የከተማዋን አዳዲስ የመዝናኛ ስፍራዎች ከቤተሰብ ጋር መጎብኘት አንዱና ዋነኛው እየሆነ መጥቷል፡፡
አዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ውብ እና ማራኪ ገጽታ እየተላበሰች ትገኛለች። የዚህ ለውጥ ዋነኛ ሞተር ደግሞ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ነው። ይህ ፕሮጀክት የመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ ሳይሆን የከተማዋን ነዋሪዎች የአኗኗር ዘይቤ፣ የማህበራዊ ግንኙነት ባህል እና የመዝናኛ ምርጫዎችን የቀየረ ትልቅ እድል ሆኗል። በተለይም እንደ ገና፣ ኢሬቻ፣ ጥምቀት እና ፋሲካ ባሉ ታላላቅ በዓላት ወቅት፣ እነዚህ የኮሪደር መንገዶችና የመዝናኛ ቦታዎች ነዋሪዎች ከቤታቸው ወጣ ብለው በነጻነት የሚዝናኑባቸው፣ ፎቶ የሚነሱባቸው እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው ቀዳሚ ስፍራዎች ሆነዋል።
በአጠቃላይ የገና እና ጥምቀት በዓላትን ጨምሮ ሌሎች በዓላትን ከቤት እና ከቤተ-እምነት ባለፈም በአዲስ አበባ የመዝናኛ ስፍራዎች በመዝናናት ማክበር እየተለመደ መጥቷል፡፡ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ማራኪ አድርጓታል። እነዚህ ስፍራዎች በተለይም በበዓላት ወቅት የደስታ እና የመዝናኛ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። ነዋሪዎች ከቤት ወጣ ብለው ንጹህ አየር እየተነፈሱ፣ ፎቶ እየተነሱና በእግር እየተጓዙ የሚያሳልፉት ጊዜ የአዕምሮ እረፍት ከመስጠቱም በላይ ለከተማዋ አዲስ ህይወት ዘርቷል። ለበዓላት ደግሞ ተጨማሪ ድምቀትን አጎናጽፏል፡፡ ወጣት ኤልያስ ተስፋ፣ “ዘንድሮውም ከሰዓት በኋላ አዲስ ከተሰሩ የመዝናኛ ስፍራዎች በአንዱ እየተዝናናሁ የገና በዓልን የማክበር እቅድ አለኝ” ሲል ሃሳቡን አጋርቷል፡፡
በጊዜው አማረ