በራስ አቅም የሚተገበር የሥራ ላይ ልምምድ

You are currently viewing በራስ አቅም የሚተገበር የሥራ ላይ ልምምድ

• በመርሃ ግብሩ 3 ሺህ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ይሆናሉ

• ለዚህ ተግባር ከተማ አስተዳደሩ ከ145 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቧል

• በተመረጡ 20 ወረዳዎች ላይ ከሕዳር 1 ቀን 2018 ጀምሮ በመተግበር ላይ ነው

“ሥራ ለሠሪው፤ እሾህ ላጣሪው” ይባላል፡፡ ሥራ፤ የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ ኑሮን መቋቋሚያ ምርኩዝ ነው። ሥራ ያስከብራል፡፡ ሥራ ያኖራል፡፡ ሥራ ያጠነክራል፡፡ ሥራ ከጥገኝነት ነፃ ያወጣል። ብዙ ጥቅምን የሚያስገኘው ሥራ፣ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣ ሠራተኛን ይፈልጋል። የሥራ ብዛትን በዓይነትም በስፋትም መፍጠር የሚችሉ ፀጋዎች የቱንም ያክል ቢትረፈረፉ፤ ሥራና ሠራተኛን ማገናኘት ካልተቻለ ውጤቱ “ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ” መሆኑ አይቀርም፡፡

ኢትዮጵያ ወጣቶቿ ሙሉ ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ክህሎታቸውንና ያላቸውን ጥሪት በሥራ ላይ እንዲያውሉላት ትፈልጋለች፡፡ ፍላጎቱ የሀገር ብቻ ሳይሆን የወጣቱ፤ በተለይም ሥራ አጥ የሆነው የህብረተሰብ ክፍል ጭምር ነው፡፡ የሥራ ፍላጎቱ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ “ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር” በሀገራዊ ቁልፍ አጀንዳነት ተይዞ ለተፈፃሚነቱ በርካታ ጥረቶች መደረግ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። እንደ ሀገር ለሥራ ዕድል መፍጠሪያነት የሚያግዙ ፀጋዎችን በጥናት በመለየት ዜጎች እንዲሰማሩባቸው ተደርጓል፤ ተግባሩም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ እየተተገበሩ ካሉ በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ አማራጮች መካከል፡- ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ይጠቀሳል፡፡

ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ትኩረቱን በወጣቶች ላይ በማድረግ፣ ሥራ ለሌላቸው ወጣቶች የሥራ ላይ ስልጠና በመስጠት ቋሚ የሥራ ዕድል የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያመቻች ነው፡፡ ይህ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ ሲተገበር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ስለ መርሃ ግብሩ አጀማመር እና ስላስገኘው ውጤት ማብራሪያ የሰጡን በአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰብሀዲን ሱልጣን እንዳብራሩት፤ በ2014 በጀት ዓመት የጀመረው መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ መንግስት እና በዓለም ባንክ ትብብር 49 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የመርሃ ግብሩ የመጨረሻው ምዕራፍ የሆነው ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. በይፋ ተጠናቅቋል። በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ 15 ሺህ ወጣቶች ተሳትፈዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም 9 ሺህ 615ቱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ወጣቶች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ተጠቃሚዎች የውጭ ሀገር ዜጎች ሆነው በስደት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡

የመርሃ ግብሩ መጨረሻ በሆነው የሦስተኛ ዙር የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ከተሳተፉ እና የስድስት ወራት ቆይታቸውን በአግባቡ ያጠናቀቁ ከስምንት ሺህ በላይ ወጣት የመዲናዋ ነዋሪዎች፤ በአሁኑ ወቅት  በተለያዩ ተቋማት እና ድርጅቶች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው እንዲሁም በግላቸው ወይም በመደራጀት የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ብዙዎች ስለመሆናቸው አቶ ሰብሀዲን አስረድተዋል፡፡

የዳይሬክተሩን ሃሳብ በመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶችም ያረጋግጣሉ፡፡ ወጣት አየናቸው ሽብሩ እና ወይዘሮ ብርቱካን ተቻለ በሮሰን ጨርቃ ጨርቅ አምራች እና የህትመት ስራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ተቀጥረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሁለት ሥራ አጥ የነበሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በድርጅቱ ቋሚ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ድልድይ የሆናቸው ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ስለመሆኑ አልሸሸጉም። በመርሃ ግብሩ ከመታቀፋቸው አስቀድሞ የነበራቸው  ሕይወት በውጣ ውረድ የተሞላ፣ ያቋረጡትን ትምህርት ለመቀጠል እንዲሁም ሠርተው ለመለወጥ የሚችሉበት መንገድ ጠፍቷቸው በቤተሰብ ጥገኝነት እንዲቆዩ የተገደዱበት፣ ለጭንቀት እና ለመብሰልሰል የተዳረጉበት እንደነበር ሩቅ ካልሆነው የትዝታ ማህደራቸው አስቃኝተውናል፡፡

ወጣት አየናቸው እና ወይዘሮ ብርቱካን በአሁኑ ወቅት በሮሰን ጨርቃ ጨርቅ አምራች እና የህትመት ስራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ብቁ ሙያተኛ ሆነው፣ በቋሚ ሠራተኛነት ተቀጥረው ገቢ ማግኘት ከጀመሩ ወራትን አስቆጥረዋል። በአራዳ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኝና 354 ካሬ ላይ ባረፈ የማምረቻ ሼድ ውስጥ ነው ሥራውን እያከናወነ የሚገኘው የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፍቅሬ ታፈሰ፤ በድርጅታቸው ከሚሠሩ 56 ባለሙያዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት፤ በብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር አማካኝነት ለስድስት ወር የሥራ ላይ ልምምድ ሲያደርጉ የቆዩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ፤ በግርማ፣ ሕይወትና ጓደኞቻቸው የእንጨት እና ብረታ ብረት ሥራ ድርጅት ውስጥ ለስድስት ወራት የቆየውን የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ በማጠናቀቅ በቋሚነት የሥራ ዕድልን ማግኘት የቻሉት ወጣቶችም የመርሃ ግብሩን ውጤታማነት በተጨባጭ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ወጣት አብርሃም ተስፋዬ እና ወጣት ዮሀንስ ጌትነት በዚህ ድርጅት ውስጥ፤ በዓለም ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግስት የጋራ ትብብር ሲተገበር በቆየው የመጨረሻው ምዕራፍ የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ተሳታፊዎች መካከል የመሆን ዕድልን አግኝተው ተጠቅመዋል፡፡ በቆይታቸውም ጥሩ ሙያዊ ብቃትን፣ የሥራ ስነ ምግባርን፣ ከቤት ውጪ ያለውን የሕይወት ልምድ በማግኘት የተሟላ የሥራ ሰው ስብዕናን የሚገነባ እርሾ መያዛቸውን መስክረዋል። በቋሚነት ከሚያገኙት ደምወዝ ባሻገር በትርፍ ሰዓታቸው በሚሠሩት ሥራ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠሩንም አንስተዋል፡፡

ከስምንት ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ከጠባቂነት በማላቀቅ ሠራተኛ እና አምራች በማድረግ የማይተካ ሚናን የተጫወተው፣ በዓለም ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር ሲተገበር የቆየው የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ጥቅምት 30 ቀን 2018 ዓ.ም. በይፋ ተጠናቅቋል፡፡ የመርሃ ግብሩ መጠናቀቅ ተስፋ ሰጪ ጅምሩን እንዳያቀጭጨው የከተማ አስተዳደሩ ቁርጠኛ አቋምን በመያዝ በራስ አቅም የሚቀጥልበትን አሠራር ዘርግቶ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ ከአምስት ዓመቱ አፈጻጸም ልምድና ተሞክሮ በመቅሰም፣ የመዲናዋን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሥራ ላይ ልምምድ እያከናወነ ይገኛል፡፡ በራስ አቅም ስለሚተገበረው የሥራ ዕድል መፍጠሪያ መርሃ ግብር አስመልክቶ አቶ ሰብሀዲን ሱልጣን ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ሰብሀዲን ገለፃ፤ በመንግሥት የሚተገበረው ብቃት የሥራ ላይ ልምምድ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተመረጡ 20 ወረዳዎች ላይ ከሕዳር 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በመተግበር ላይ ነው፡፡ በራስ አቅም የሚከናወነውን ብቃት የሥራ ላይ ልምምድ ለማስፈፀም በከተማ አስተዳደር ደረጃ ከ145 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በዚህ መርሃ ግብር 3 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሕዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እየተሠራ ይገኛል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 34 የሚገኝ፣ የትምህርት ዝግጅታቸው ከ12ኛ ክፍል በታች የሆነ፣ ሥራ የሌላቸው ወይም የሚሠሩትን ሥራ በተለያየ ምክንያት አቋርጠው ቤታቸው የተቀመጡ ሲሆኑ፤ ከመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች መካከል የሴቶች ድርሻ 60 ከመቶ የሚይዝ ይሆናል፡፡

“በብቃት የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር የሚሳተፉ ወጣቶች በዋናነት ሙያዊ ክህሎትና ዕውቀት ሊያገኙባቸው ወደሚችሉ ተቋማት ወይም ድርጅቶች ልምምድ ያደርጋሉ፡፡ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶቹን ተቀብለው የሥራ ላይ ልምምድ እንዲያደርጉ ዕድል የሚሰጡ 1 ሺህ የሚሆኑ ተቋማት ወይም ድርጅቶች ተለይተዋል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ብቃት የሥራ ላይ ልምምድን ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉ መሆናቸው ተቋማዊ በሆነ አሠራር ልየታ እና ማረጋገጫ የተሰጣቸው ናቸው” ያሉት የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተሩ፤ ወጣቶቹም ወደ ድርጅቶቹ የሚሄዱት በፍላጎታቸው መሰረት መሆኑን በመጥቀስ ድርጅቶቹን ከመቀላቀላቸው በፊት ለ12 ቀናት የሚቆይ የሕይወት ክህሎት እና የሥራ ማፈላለግ ስልጠና እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፤ ለሥራ ላይ ልምምድ በሚሄዱባቸው ድርጅቶች ላይ ማሳየት ስለሚገባቸው የሥራ ላይ የስነ ምግባር ስልጠና ተሰጥቷቸው፣ ወደ ድርጅቶቹ ለመግባት የሚያስችላቸውን ቅድመ ሁኔታ ሲያሟሉ ከድርጅቶቹ ጋር ውል ፈፅመው የሥራ ላይ ልምምዳቸውን እንደሚጀምሩ ጠቁመው፤ “በድርጅቶቹ እና የሥራ ላይ ልምምድ በሚያደርጉ ወጣቶች መካከል የሚፈጸመው ውል ለስድስት ወራት ይቆያል፡፡ ወጣቶቹ የድርጅቱን የሥራ ባህል በማክበር፣ የሠራተኛ ስነ ምግባርን ተፈፃሚ በማድረግ የሥራ ላይ ልምምዱን ባልተቆራረጠ ሁኔታ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ድርጅቶቹም ለሥራ ላይ ተለማማጆች ዕውቀትና ክህሎት ሊያስጨብጥ በሚችል አግባብ ምቹ የሥራ ቦታ፣ የሥራ መሣሪያን፣ ግብዓትን በማሟላት ወጣቶቹን የበቁ ሙያተኞች የማድረግ ኃላፊነትን መወጣት ይገባቸዋል፡፡ ይህ የሥራ ላይ ተለማማጅ ወጣቶች እና የድርጅቶች ግንኙነት በአጠቃላይ ለስድስት ወራት የሚቆይ ሲሆን፤ እንደ መደበኛው የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት በቀን ለስምንት ሰዓታት፣ በሣምንት ለአምስት ቀናት፣ በወር ለሀያ ሁለት ቀናት ተፈጻሚ ይሆናል” በማለት አብራርተዋል።

በብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር የታቀፉ ወጣቶች የሚለማመዱባቸው ድርጅቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን ከዘርፎቹ መካከልም፡- የአምራች (ማንፋክቸሪንግ)፣ የግንባታ (ኮንስትራክሽን)፣ የአገልግሎት (ሰርቪስ)፣ የንግድ እንዲሁም የከተማ ግብርና ዘርፎች  በዋናነት ይጠቀሳሉ። በእነዚህ ድርጅቶች ለስድስት ወራት በሚቆየው ብቃት የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ላይ ለሚሳተፉ 3 ሺህ ወጣቶች፤ ለትራንስፖርት አገልግሎት ወጪ የሚሆን ገንዘብ በቀን 149 ብር በማሰብ መንግስት ለእያንዳንዳቸው በየወሩ ክፍያ የሚፈፅም መሆኑን ከሥራና ክህሎት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

አቶ ሰብሃዲን በሰጡት ማብራሪያ እንዳስታወሱት፤ ከዚህ ቀደም በከተማ አስተዳደር ደረጃ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በተተገበረው ብቃት የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ሂደት ውስጥ በርካታ ልምድና ተሞክሮዎች ተገኝተዋል። ለምሳሌ፤ ድርጅቶች የሚቀርቡላቸው የብቃት የሥራ ላይ ተለማማጅ ወጣቶች በሥራ ላይ ያላቸውን ሙያዊ ብቃት እና ውጤታማነት በማየት የተለያየ የማበረታቻ ተጠቃሚ ያደርጓቸዋል። ተጨባጭ ክህሎትና ዕውቀት እየያዙ በዚህ ሂደት ውስጥ ማለፋቸው አብዛኛው በሚባል ደረጃ በአራት ወር ውስጥ ብቁ ሠራተኛ ሆነው ከድርጅቶች ጋር በቋሚነት ለመሥራት የሚያስችል ውል እስከ መፈራረም ይደርሳሉ፡፡ በአራት ወራት ቆይታቸው ብቻ በወር እስከ 10 ሺህ ብር ገቢ ማግኘት የቻሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ወርሃዊ ደምወዝ ከ30 ሺህ ብር በላይ በሚያስገኝ ሥራ ላይ ተቀጥረው የሚሠሩም አሉ፡፡

በራስ አቅም ተግባራዊ መደረግ በጀመረው የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ላይ ስለሚከናወኑ መሰረታዊ ተግባራት በተመለከተ አቶ ሰብሀዲን ሲያብራሩ፤ “ወጣቶቹ በመርሃ ግብሩ ታቅፈው ለስድስት ወራት በሥራ ላይ ልምምድ ቆይታ ሲያደርጉ፤ ሙያን ብቻ አይደለም የሚቀስሙት፡፡ የሥራ ስነ ምግባርን በተግባር ይለማመዳሉ፡፡ የእርስ በእርስ የአቻ የሥራ ላይ ውይይት ቢያንስ በየወሩ ያደርጋሉ፡፡ የአቻ ለአቻ ውይይት እና ምክክሩ በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ባሉ የሥራ ላይ ተለማማጅ ወጣቶች ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በተለያየ ድርጅት ውስጥ ያሉ ወጣቶች በጋራ ተገናኝተው ልምድና ተሞክሯቸውን እንዲለዋወጡ ይደረጋል፡፡

ወጣቶቹ የስድስት ወራት የሥራ ላይ ልምምድን በብቃት አጠናቅቀው ሲመረቁ ለቀጣይ ሥራቸው ማስረጃ ሆኖ የሚያገለግላቸው ሦስት ዓይነት የምስክር ወረቀት (ሰርተፊኬት) ይሰጣቸዋል፡፡ የመጀመሪያው የምስክር ወረቀት የሕይወት ክህሎት ስልጠና መውሰዳቸውን የሚያረጋግጥ ሲሆን፤ ሁለተኛው መሠረታዊ የኮምፒዩተር ስልጠና መውሰዳቸውን የሚገልፅ ነው። ዋናውና ሦስተኛው ደግሞ የሥራ ላይ ልምምድ ያደረጉበት ተቋም ወይም ድርጅት የሚሰጣቸው የስድስት ወር የሥራ ላይ ልምድ(experience)  ነው። በዕውቀት፣ በክህሎት፣ በሥራ ስነ ምግባር፣ በአስተሳሰብ ለውጥ ያሳዩት እነዚህ ወጣቶች በመጨረሻ የተቀበሏቸውን የምስክር ወረቀቶች ይዘው ልምምድ ባደረጉበት ድርጅት መቀጠር፣ ሌላ ድርጅት ፈልገው ተወዳድረው መግባት፣ በግላቸው ወይም በመደራጀት የራሳቸውን ሥራ መጀመር ይችላሉ” ብለዋል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review