ልጆች “አሲና በል አሲና ገናዬ…! እየተባለ የሚገጠመው መቼ እንደሆነ ታውቃላችሁ? ለገና በዓል እንደምትሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እንኳን ለበዓሉ በሰላም አደረሳችሁ! እያልኩ ስለገና ጨዋታ ምንነት፣ ጨዋታውን ስንጫወት ስለምንጠቀማቸው ቁሳቁሶች እንዲሁም በጨዋታው ላይ ስለሚገጠሙ ግጥሞች ለእናንተ ለልጆች ማብራሪያ እንዲሰጡልን አንድ እንግዳ ጋብዘናል፡፡
መስፍን ከበደ እባላለሁ፡፡ በአዲስ አበባ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ እና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነኝ፡፡ የገና በዓል እረኞች የኢየሱስ ክርስቶስ ልደትን ምክንያት በማድረግ የገና ጨዋታን ከታህሳስ ጀምሮ እስከ ጥር ከዚያም እስከ ክረምቱ መግቢያ ይጫወቱት እንደነበር የቀድሞ አባቶች ይናገራሉ። ጨዋታው የሚካሄደውም አርሶ አደሮች ሰብላቸውን ከሰበሰቡ በኋላ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ ነው፡፡
ልጆች የገና ባህላዊ ጨዋታ የሚካሄደው በሁለት ቡድኖች መካከል ነው፡፡ ተጫዋቾች ወደ ሜዳ የሚገቡት “አሲና በል አሲና ገናዬ…” በማለት በአንዱ ቡድን 10፣ በሌላው ቡድን 10 በመሆን ነው፡፡ ቡድኖቹ የየራሳቸው በረኛ ወይም ጠባቂ አላቸው፡፡ ጨዋታው አንድ ዋና፣ ሁለት የመስመር እና አንድ የነጥብ መዝጋቢ ዳኞች አሉት፡፡ በጨዋታው ወቅት ልክ እንደ እግር ኳስ የራሱ የማዕዘን ምት እንዲሁም የቅጣት ምት የሚሉ የጨዋታ ህጎች አሉት፡፡
ልጆች የገናን ጨዋታ ስንጫወት ከምንገለገልባቸው ቁሶች ሩር ወይም ጥንግ አንዱ ነው፡፡ ይህ ቁስ በገጠሩ የማህበረሰብ ክፍል ከጠፍር ወይም ከጉቶ ተጠርቦ የሚሰራ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከፕላስቲክ እንደ ኳስ መስራትም ይቻላል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ሩሯን የምንመታበት ዱላ ነው፡፡ ዱላው ጫፉ ላይ ጠመም ያለ ቅርፅ ያለው ሲሆን፤ ይህም ሩሯን እንዳስፈለገ ለመምታትና ወደ ሌላ ቦታ እንዳትሄድ ለመመለስ የሚረዳ መሳሪያ ነው፡፡
ልጆች ኳስ ስትጫወቱ ጎል እንዳለ ሁሉ የገና ጨዋታም ሩሯ እንዳትሾልክ የሚያደርግ ከሸራ ወይም ከማዳበሪያ እንደመረብ የተሰራ ጎል አለው፡፡ 60 ደቂቃ የጨዋታ ጊዜ ያለው ሲሆን፤ አቻ ስትሆኑ አንድ፣ አሸናፊ ከሆነ ደግሞ ሶስት ነጥብ ያገኛል፡፡ ይህም ማለት አሸናፊና ተሸናፊም አለው ማለት ነው፡፡
ልጆች የገና ጨዋታ ባህላችንን ለማስተዋወቅና ኢትዮጵያን ለመግለፅ ተጫዋቾች እግረ ጠባብ እና ራሳቸው ላይ ሻሽ አስረው ነው የሚጫወቱት፡፡ የዱሮ አባቶች ሲጫወቱ ለመጫወት ፍላጎት ያለው ትልቅ ትንሽ፣ አሰሪም ሰራተኛ ሳይል ሁሉም እኩል ይጫወት ነበር፡፡ ይህንን ምሳሌ በማድረግም “በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፣ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እየተባለ ግጥሞች ይገጠማሉ፡፡ ይህ ማለት በዚህ ጨዋታ ትልቅ ትንሽ ሳይባል አንዱ በአንዱ ላይ ጉዳት እንኳን ቢያደርስ ቅጣትም ሆነ ቂም አይያዝም ማለት ነው፡፡
እናንተም ልጆች ከገና ጨዋታም ውጭ ቢሆን ከጓደኞቻችሁ ጋር ስትጫወቱ አንዱ አንዱን ቢጎዳው ወይም በኳስ ቢመታው ሳትኮራረፉ፣ ቂም ሳትይዙ ተግባብታችሁ በፍቅር መጫወት አለባችሁ፡፡
ልጆች የገና ጨዋታ ለመጫወት ወደ ሜዳ ሲገባ ተቃራኒ ቡድኖች ዱላቸውን አጣምረው ወይም የኤክስ ምልክት ሰርተው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየው አንድነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅር፣ እንዲሁም ስፖርት የሰላም መድረክ መሆኑን ለመግለፅ ነው፡፡
የገና ጨዋታን አያቶቻችን እና አባቶቻችን ሲጫወቱት የነበረ አሁንም ያለ በመሆኑ እናንተም የሀራችሁን ባህልና ወግ ለማወቅ መጫወት አለባችሁ፡፡ እናንተ የፈረንጆቹን ጨዋታ አስበልጣችሁ እንድታዩና እንድትወዱት ያደረጋችሁ እነሱ የራሳቸውን ወግና ባህል ስለሚያስጠብቁ ነው፡፡ ስለዚህ የራሳችሁን ወግና ባህል በማወቅ መኩራት እና በተግባርም ማሳየት አለባችሁ፡፡
ልጆች በገና ጨዋታ፣ በትግል፣ በገበጣ፣ በፈረስ ጉግስ እንዲሁም ቀስትና በመሳሰሉት ባህላዊ ጨዋታዎች በመወዳደር ስፖርቶቹን ወደ ኦሎምፒክ ማስገባትና ኢትዮጵያን ማስጠራት ትችላላችሁ፡፡ ባህልና ወጋችሁን የምትወዱ መሆን አለባችሁ፡፡ መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ፡፡ ሰላም ሁኑ ልጆች፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ