“ሙዚየሙን ሁለት ሶስት ጊዜ እየዞርኩ አየሁት፤ ያየሁት ነገር በጣም አስደንቆኛል”
ከሳዑዲ አረቢያ የመጣው ወጣት ኢብራሂም ጋታኔ
ወይዘሮ ሂሩት ነጋሽ ይባላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ቅርሶችን ሲጎበኙ ነው ያገኘናቸው፡፡ “ማንኛውም ሰው ገብቶ መጎብኘት እንደሚችል አላውቅም ነበር፡፡ አድራሻውን በዩቲዩብ ስመለከት ታሪኬን ለማወቅ ልጆቼን ይዤ ለጉብኝት መጣሁ” ይላሉ፡፡
“የሚታየው ነገር ቀልብን ይስባል፤ የእንግዳ ተቀባዮቹ ትህትናም ይማርካል። ውጭውን ሳየው አዲስ አበባ ሳይሆን ውጭ ሀገር ያለሁ ነው የመሰለኝ፡፡ ወደ ውስጥ ስንገባ ደግሞ ተማሪ ሆኜ የማደንቃትን ሉሲን በአይኔ አየኋት። የእንስሳት ቅሪተ አካል ጥንታዊ መመገቢያና መጠጫ ቁሳቁሶች፣ ስእሎችና ሌሎችንም ጎብኝቻለሁ፡፡ ቅርሶቹ በዚህ መንገድ መቀመጣቸው የኢትዮጵያን ገናና ታሪክና ምድረ ቀደምትነት በአግባቡ ለማሳየት ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
“አሜሪካ ሀገር በሄድኩበት አጋጣሚ በዚያ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሙዚየም አይቻለሁ፤ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየምን ስላየሁት እንዲህ ቢሆን ብዬ ተመኝቼ ነበር፡፡ አሁን ስጎበኘው ግን የበለጠ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ብዙ ቅርሶች የያዘም ነው፡፡ ታሪካችን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአለምም የሚተርፍ ነው፡፡ በዚህ መልክ ተደራጅቶ በአግባቡ በእንክብካቤ መያዙ ታሪክን ህያው እንዲሆን የሚያደርግ ነው፡፡ ለሌሎች አካላትም በኩራት ያየሁትን እንድናገር ያደርገኛል” ሲሉ የልባቸው መሻት እውን እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ሌላኛው በሙዚየሙ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ሲጎበኝ ያገኘነው ከሳዑዲ አረቢያ የመጣው ወጣት ኢብራሂም ጋታኔ ነው፡፡ “ሙዚየሙን ስጎበኝ የመጀመሪዬ ነው፡፡ ሁለት ሶስት ጊዜ እየዞርኩ አየሁት፤ ያየሁት ነገር በጣም አስደንቆኛል” ሲል የተመለከተው ነገር የፈጠረበትን ስሜት ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ግቢው ሳቢ፣ ለጎብኚዎችም ምቹ መሆኑንም አክሏል፡፡
ወይዘሮ እኙዋማከ አግቦ ሌላኛዋ ከናይጀሪያ የመጡ ቱሪስት ናቸው። ሙዚየሙን ሲጎበኙ የመጀመሪያቸው መሆኑንም ነግረውናል፡፡ “በሙዚየሙ የሰው ዘር ቅሪተ አካል የሆነችው ሉሲን አይቻለሁ፡፡ በፊት የነበሩትን የኢትዮጵያ ነገስታት ታሪክን ተመልክቻለሁ። የተለያዩ ታሪክ ያላቸው አልባሳትም አሉ። እነዚህንም በመጎብኘቴ ደስ ብሎኛል። የሙዚየሙ ግቢም አረንጓዴ ነው፡፡ ብዙ ታሪክ አላችሁ፡፡ ሌላ ጊዜም መጥቼ እጎበኛለሁ፡፡” ሲሉም በሙዚየሙ የነበራቸውን የጉብኝት ቆይታ እንደወደዱት ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
የዝግጅት ክፍላችንም ባደረገው ቅኝት፣ ታሪክን ከውበት ጋር አጣምሮ የያዘው ሙዚየም ከውጭ ሲገቡ አበቦቹ እይታን ከመሳብ አልፈው መአዛቸው ከሩቅ የሚጣራ፣ መሬቱን አረንጓዴ ያደረገው ለምለም ሳር፣ የደከመው የሚያርፍባቸው ወንበሮች፣ መኪና ማቆሚያ ምቹና ሰፊ ቦታ፣ ከሩቅ አይንን ሰቅዞ የሚይዘው ፋውንቴን እንዲሁም የህንፃው ቀለም የጎብኚዎችን ቀልብ ለመያዝ ትልቅ አቅም እንደሆኑት መረዳት ችሏል፡፡ “ደጅአፏን አይተህ ከቤቷ ግባ…” እንዲል የሀገራችን ብሂል የውጭው ውበት የውስጡን ለማየት ጉጉትን የሚያጭር ሆኖ አግኝቶታል።
ወደ ውስጥ ሲገባም ቅርሶቹ ደረጃውን ጠብቆ በታደሰው ቦታ በየፈርጃቸው ህያውነታቸውን ለማመስከር ለጎብኚዎች ምቹ ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ በተለየ ሁኔታ የውጭ ጎብኚዎች እጃቸውን አፋቸው ላይ ጭነው በትኩረት ሲመለከቷቸው መታዘብ ችሏል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የትምህርት ዴስክ ኃላፊ አቶ ንጉሱ መኮንን ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፤ “ሙዚየሙ እንዲታደስ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት፤ በርካታ ዓመታትን ያገለገለ በመሆኑ፣ የሙዚየሙን ውስጣዊና ውጫዊ ክፍል ደረጃውን በማሻሻል ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ እንዲሁም ኢትዮጵያ ያላትን ብዝሃ ቅርስ ለማስተዋወቅ እድል ለመፍጠር ነው” ብለዋል፡፡
በአካባቢው የተከናወነው የኮሪደር ልማትም ሆነ የውስጡ እድሳት ለሙዚየሙ የገጽታ ፍካት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው የሚናገሩት አቶ ንጉሱ፣ ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ መንገድ በግቢው ለአካል ጉዳተኞች፣ ለህፃናት እንዲሁም አረጋዊያን ማረፊያ ወንበሮች ተሰርተዋል፡፡ ለአይን የሚስብ አረንጓዴ ልማትና ፋውንቴን ያለው መሆኑ አጠቃላይ የግቢውን ገፅታ የተዋበ እንዲሆን እንዳደረገውም አክለዋል።
“በየትኛውም ዓለም ያሉ ብሔራዊ ሙዚየሞች የሚጠቀሙትን የኤግዚቢሽን አደረጃጀት ቴክኖሎጂን ተጠቅመን ማደስ መቻላችን በፊት ከነበረው የሙዚየሙ ገፅታ ላይ ውበት እንዲጨምር አድርጓል። ቅርሶቹ በጽሑፍ እንዲሁም በስዕላዊ መረጃ በግልፅ መቀመጣቸው ጎብኚዎቹ ታሪኩ ገብቷቸው እንዲጎበኙ እና ደስተኛ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ንጉሱ ገለጻ፣ የታሪክና የአርኪዮሎጂ ስብስብ ክፍሉ እንዲሁም የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ እና የእንስሳት ቅሪተ አካል የሚታይበት ክፍል ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ታድሶ ተጠናቅቋል፡፡ ቀሪዎቹን የብሔር፣ ብሔረሰቦች ባህል፣ አኗኗር፣ ታሪክ እንዲሁም የሥነ ጥበብ ውጤቶች የሚታዩበት ሁለት ክፍሎች ከታደሱት ጋር በተናበበ መልኩ በሂደት ይታደሳሉ፡፡ እነዚህ ክፍሎች ታድሰው ለአገልግሎት ሲበቁ ሙዚየሙ ከበፊቱ በተሻለ መልኩ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ጎብኚዎች እንዲሁም ተመራማሪዎች ጭምር የሚጠቅም ነው፡፡
ሙዚየሙ በቅርስ ስብስቡ ታዋቂ የሆኑ፣ ሉሲን፣ ሰላምንና አርዲን የመሳሰሉ ሀገራችን በሰው ዘር አመጣጥ ያላትን ቦታ የሚያሳዩ፣ በታሪክ፣ በባህልም ሆነ በስነ ጥበብ ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ቅርሶችን የያዘ፣ እድሳቱም ይህንን የበለጠ በሚያጎላ መልኩ የተከናወነ ነው፡፡
“የከተማ መልማትና መዘመን ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት” የሚሉት የትምህርት ዴክስ ኃላፊው፤ ለገፅታ ግንባታ፣ ለኢኮኖሚ ምንጭነት እንዲሁም ለማህበረሰቡ የሚሰጠው እርካታ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ከአየር ማረፊያ እስከ እንጦጦ ፓርክ ድረስ ያለው መንገድ የሙዚየም ኮሪደር ተብሎ ስለሚጠራ ጎብኚዎች ከአየር ማረፊያ ጀምሮ ጎብኝተው እስከሚመለሱ ድረስ በተመቻቸው መንገድ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ይህ የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ይጨምራል፤ ገቢ ያስገኛል፤ የሃገሪቱንም ሃብት መጠቀም ያስችላል ነው ያሉት፡፡
ቱሪስቶች በሚያገኙት አገልግሎት ልክ ነው ገንዘባቸውን የሚያወጡት ያሉት አቶ ንጉሱ፤ ኮሪደር ልማቱም ሆነ ከሱ ጋር ተያይዞ የታደሱና ለአገልግሎት ምቹ የሆኑ አካባቢዎች መፈጠራቸው ለብሔራዊ ሙዚየሙ ትልቅ እድል ፈጥሮለታል፡፡
የመጣው ጎብኚ እርካታ አግኝቶ፣ ጥሩ ነገር በአዕምሮው ይዞ እንዲመለስ ማድረግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ንጉሱ፣ ይህም በሂደት ለመጪው እድላችን መደላድል እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
ወርሃ ታህሳስና ጥር የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚያቅዱበት እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ቱሪዝሙን የበለጠ አጎልብቶ የኢኮኖሚ አቅምን በማሳደግ ረገድ አወንታዊ ሚና የሚጫወት ገቢን ለማግኘት እንደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ነባሮችን መዳረሻዎች ማልማት፣ አዳዲሶችን ማስፋፋትና መሰረተ ልማቶቻቸውን የተመቸ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ እየተሰራ ያለውን ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል እንላለን፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ